የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችን እየደገፈ መሆኑን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችን እየደገፈ መሆኑን አስታወቀ
አሶሳ፤ ጥቅምት 16/2016 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በክልሉ በመንግስት እየተከናወኑ ያሉ የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችን እየደገፈ መሆኑን አስታወቀ።
ማህበሩ በክልሉ አሶሳ ዞን ያከናወናቸው የአደጋ ምላሽና የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች ተጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ሞገስ ነገሮ እንደገለጹት ማህበሩ በተለያዩ ምክንያቶች ለጉዳት የተጋለጡ የማህበረሰብ ክፍሎችን መደገፍ ዋነኛ ትኩረቱ ነው።
በክልሉ ቀደም ሲል ግጭት ተከስቶባቸው በአሁኑ ወቅት ወደ ሰላም በተመለሱ አምስት የመተኮል ዞን ወረዳዎች ጽህፈት ቤቱ 390 የቆርቆሮ ክዳን መኖሪያ ቤቶችን አስገንብቶ ያጠናቀቀ ሲሆን አብዛኞቹ ለአገልግሎት መብቃታቸውንም ተናግረዋል።
ቁጥራቸው ከ2 ሺህ የሚበልጡ ተፈናቃዮችና አቅመ ደካሞችን አቅም ለማጠከርም በበግና ፍየል ማደለብ ሥራ እንዲሰማሩ ማህበሩ እገዛ ማድረጉንም አመልክተዋል።
አቶ ሞገስ እንዳሉት በአካባቢው ተከስቶ በነበረ ግጭት ለጉዳት የተዳረጉ ወገኖችን አምራች ዜጋ ለማድረግ ስነልቦናቸውን የሚያጠናክር ስልጠናም ተሰጥቷል።
በተለይ የሴቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም ለመገንባት ጥረት መደረጉንም ነው ያመለከቱት።
ከእዚህ በተጨማሪ የመጠጥ ውሃ ተቋማት በመገንባት፣ ለጤና ተቋማት ጀነሬተር፣ አልትራሳውንደና የተለያዩ የሕክምና ቁሶችን በማሟላትና የጤና ባለሙያዎች ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ ማህበሩ ድጋፍ ማድጉን አስረድተዋል።
በተራቆቱ አካባቢዎችም ማህበሩ ችግኝ ተክሎ በመንከባከብ ለዘላቂ ልማት ያከናወናቸው ሥራዎች እንዳሉ ጠቁመው፣ "በዚህም የመንግስት ክፍተቶችን የመሙላት ሃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል" ብለዋል።
ከአጎራባች ኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባምባሲ ወረዳ ከሚገኙ ከ200 በላይ ተፈናቃዮች መካከል የ18 ልጆች አባት አቶ መሃድ ኢሳ አንዱ ናቸው።
እርሳቸውና ልጆቻቸው ከቀይ መስቀል ማህበር በቋሚነት የእለት ምግብ ድጋፍ እያኙ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ባለፈው አንድ ወር በሦስት ተከታታይ ዙሮች ድጋፍ እንደተደረገላቸው ጠቁመው ይህም ቤተሰቦቻውን ለመደጎም አቅም እንደሆናቸው አስረድተዋል።
በባምባሳ ወረዳ መንደር 41 የሚኖሩት የ80 ዓመት አዛውንት አቶ ዘገየ ምስጋና በበኩላቸው፣ ማህበሩ የወደቀ የሣር ክዳን ቤታቸውን በቆርቆሮ ክዳን በመቀየር ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሃጂራ ኢብራሒም "ቀይ መስቀል በተለይም በክልሉ በመተከል ዞን እየተካሄደ ላለው የመልሶ መቋቋም ሥራ ያደረገው ድጋፍ በአርአያነት ይጠቀሳል" ብለዋል።
እንዲሁም ማህበሩ የአቅመ ደካማ ሴቶችን አቅም በቁጠባ ለማሳደግ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የጠቀሱት ሃላፊዋ፣ ማህበሩ በመልሶ ማቋቋም ሥራ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አድንቀዋል።
ሌሎች በክልሉ የሚንቀሳቀሱ አጋር አካላት ከማህበሩ ተሞክሮ በመውሰድ በመልሶ ማቋቋምና በልማት ሥራዎች እገዛ እንዲያደርጉም አስገንዝበዋል።