ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት የምታቀርበው የኃይል ሽያጭ በየዓመቱ ጭማሪ እያሳየ ነው- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 16/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት የምታቀርበው  የኃይል ሽያጭ በየዓመቱ ጭማሪ እያሳየ መምጣቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገለፀ።

በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት ካቀረበችው የኃይል ሽያጭ 21 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር ማግኘቷም ተገልጿል።

ጅቡቲ፣ ኬንያና ሱዳን የኤሌክትሪክ የኃይል ሽያጭ የተደረገባቸው አገራት ሲሆኑ ለደቡብ ሱዳንና ታንዛኒያ ኤሌክትሪክ  ኃይል ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል።

የተቋሙ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንዳሉት፤  ኢትዮጵያ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ለሱዳንና ጅቡቲ እንዲሁም ካለፈው በጀት ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ለኬንያ የኃይል ሽያጭ እያከናወነች ትገኛለች።

 የኃይል ሽያጩ በየዓመቱ እድገት እያሳየ መምጣቱን አንስተው፤  ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረው 50 ሚሊየን ዶላር በ2015 በጀት ዓመት ወደ 101 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር ማደጉን ተናግረዋል።

ተቋሙ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለሱዳን፣ ለጅቡቲና ለኬንያ ከቀረበው የኃይል ሽያጭ 21 ነጥብ 4 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ማግኘቱንም ገልፀዋል።

ከአገር ውስጥ የኃይል  ሽያጭም 4 ነጥብ 38 ቢሊየን ብር  ማግኘቱን አያይዘው ገልጸዋል።

የአገር ውስጥና የጎረቤት አገራት የሩብ ዓመት የኃይል ሽያጭ  ከእቅዱ አንፃር ሲታይ የ80 በመቶ አፈፃፀም የታየበት መሆኑንም ተናግረዋል።    

በተያዘው በጀት ዓመት መጨረሻ  ለጎረቤት አገራት የሚቀርበውን የኃይል ሽያጭ 150 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ለማድረስ መታቀዱንም ተናግረዋል።    

ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ከአገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ሺያጭ ደግሞ  20 ነጥብ 16 ቢሊየን ብር ለማግኘት ማቀዱን አስታውቀዋል።  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም