ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ስደተኞችን በማስጠለል ከዓለም አቀፋዊ ስምምነቶች ባሻገር በራሷ የስደተኞች ፖሊሲ በመመራት ቀዳሚነቷን አረጋግጣለች - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2016(ኢዜአ)፦  ኢትዮጵያ ስደተኞችን በማስጠለል ከዓለም አቀፋዊ ስምምነቶች ባሻገር በራሷ የስደተኞች ፖሊሲ በመመራት ቀዳሚነቷን ማረጋገጥ መቻሏን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡  

በስዊዘርላንድ ጀኔቭ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የስደተኞች ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ የምታቀርበውን ስድስት አዲስ የቃል ኪዳን ሰነድ ለማጽደቅ የተዘጋጀ የከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኛ በማስጠለል የሚከሰተውን የተፈጥሮ ሀብት ውድመት መልሶ ለማልማት ከ100 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ዝርያ ያላቸው ችግኞችን መትከሏን፤ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ከብሔራዊ የኤሌክትሪክ ግሪድ ጋር በማስተሳሳር የታዳሽ ኋይል እንዲጠቀሙ ማድረግ ና  የስደተኞች ጉዳይ  ከብሄራዊ  ዕቅድ ውስጥ ማካተት የቃል ኪዳኑ አካል ነው ተብሏል፡፡

እኤአ እስከ 2027 በተመረጡ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎችን መንገድ፣ መብራት፣ ውኃ፣ የአካባቢ ንፅህና፣ ጤና እና ትምህርት መሠረተ ልማቶችን በማሟላት ከአጎራባች ከተሞች ማስተር ፕላን ጋር በማገናኘት ወደ ዘላቂና ምቹ ከተማነት ማሳደግ ሌላኛው ነው፡፡

አንድ ሚሊዮን ስደተኞችን በብሄራዊ ፕሮጀክቶች ማካተት፣ 800 ሺህ ስደተኞችን የብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም  ማካተት፣  የሁለተኛ ደረጃ የስደተኞች ትምህርት  መስጠት እንዲሁም 30 ሺህ ስደተኞችንና ተቀባይ ማህበረሰብን በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ማካተት  ከሰለጠኑት ውስጥ ለ70 በመቶ የስራ ዕድል መፍጠር የቃል ኪዳኑ ሶስተኛ ሀሳብ ነው።

ሌላው በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች እና በአካባቢው የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማሳደግ የስደተኞችና ተቀባይ ማህረሰቦችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት ማጎልበት እና ምርታማነታቸውን ማሳደግ የሚል ነው፡፡

10 ሺህ ሄክታር የመስኖ መሬት በሊዝ በማቅረብና የተቀናጀ የግብርና እና የእንስሳት ልማትን በመተግበር የስደተኞችና ተቀባይ ማህበረሰብ የምግብ ዋስትና እና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ፤ ከዕድሉ ተጠቃሚዎች 30 ሺህ ስደተኞች 50 በመቶ ሴቶች እንዲሆኑ ማድረግ ነው ተብሏል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ከ1 ሚሊየን በላይ ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ላይ ትገኛለች ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞችም ስድስቱ ቃል ኪዳኖች ገቢራዊ ተደርገውላቸው ከማህበረሰቡ ጋር ተቆራኝተው መኖር የሚችሉበትን እድል ያጠናክራል ብለዋል።

እኤአ በ2019 በተካሄደው ዓለም አቀፍ የስደተኞች ጉባኤ ላይ አራት ቃል ኪዳኖችን በትምህርት፣ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና፣ በማዕድንና መሰል ዘርፎች በማቅረብ ውጤታማ ስራ ማከናወኗንም አስታውሰዋል።

በአራቱ ቃል ኪዳኖች ያስመዘገበችውን ስኬት በቀጣይ ታህሳስ ወር በሚቀርቡት ስድስት ቃል ኪዳኖች መድገም የሚያስችል እንቅስቃሴ እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም በታህሳስ 2023 በስዊዘርላንድ ጀኔቭ  በሚካሄደው የዓለም የስደተኞች ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ የምታቀርበው አዲስ ቃል ኪዳን በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞች ከማህበረሰቡ ጋር የበለጠ ተቆራኝተው መኖር የሚችሉበት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ያላት የላቀ አፈፃፀም ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው ስደተኞችን ተቀብሎ በማስተናገድም ያላት ሚና የጎላ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘብ እንደሚገባ  አስረድተዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተከሰቱ ዓለም አቀፍና ሀገራዊ ጫናዎችን ውስጥም ሆና 120 ሚሊየን ህዝቦቿ ጋር ከ1 ሚሊየን ስደተኞችን ማስተናገዷ ታላቅነቷን የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፋዊ ስምምነቶች፣ መርሆዎችና ማዕቀፎች ባሻገር በራሷ የስደተኞች ፖሊሲ በመመራት በዘርፉ ከዓለም ቀዳሚነቷንና ቁርጠኝነቷን እያሳየች መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡


 

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሀሰን፤ በአየር ንብረት ለውጥ በጦርነትና መሰል አደጋዎች በዓለም ዙሪያ ያሉ ከ110 ሚሊየን በላይ ዜጎች ተፈናቅለው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ አስታውሰዋል፡፡

ከእነዚህ መካከል 35 ሚሊየን የሚሆኑት ስደተኞች ሲሆኑ ስድስት ሚሊዬን የሚሆኑት ደግሞ ጥገኝነት ጠያቂዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያም በ26 የመጠለያ ጣቢያዎች ከ1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ተቀብላ እያስተናገደች መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የስደተኞች መብትና ጥበቃን ማስከበር የሚያስችል ተራማጅ የህግ ማዕቀፍ አዘጋጅታ ለስደተኞች የላቀ መብት ከሚሰጡ ሀገራት ተርታ ተመድባለች ብለዋል፡፡

የስደተኞች ጉዳይ ግን ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው በመሆኑ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብር መፍጠር ይገባል ነው ያሉት።


 

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር የኢትዮጵያ ተወካይ አንድሪው ምቦጎሪ፤ ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት በስደተኞች አያያዝ ላይ ያሳየችው ቁርጠኝነት ለቀጣናው ሀገራት መሰረት የሚሆን ነው ብለዋል፡፡

የስደተኞችን ጥበቃ በማረጋገጥ፣ በገበያ ትስስር፣ የኑሮ ሁኔታቸውን በማሻሻል፣ ትምህርትና ስልጠና በመስጠት ያደረገችው እንቅስቃሴ ሁነኛ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለውን የስደተኞች አያያዝ በቅርበት እንደሚከታተሉት የገለጹት አንድሪው ምቦጎሪ፤ በቀጣይ ታህሳስ ወር ለሚቀርበው ቃል ኪዳን ተፈፃሚነት ተቋማት አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል፤ እኛም ለማገዝ ቁርጠኛ ነን ብለዋል፡፡


 

የኢጋድ የጤናና ማህበራዊ ልማት ዳይሬክተር ማዳም ፈቲያ አልዋን፤ የኢጋድ አባል ሀገራት እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስደተኞችን፣ የመላሾችና ተቀባይ ማህበረሰቦችን በተመለከተ ቀጣይነት ያለው የመፍትሔ ሀሳብ ማቅረብ አለባቸው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በመጀመሪያው የዓለም አቀፍ የስደተኞች ኮንፈረስ ከአፍሪካ ብቸኛዋ ሀገር እንደነበረች አስታውሰው ኢጋድ በሀገሪቱ የሚከናወነውን የስደተኞች አያያዝ ለመደገፍ ፈጣን የተግባር እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም