የጌዴኡፋ ቋንቋ የመዝገበ ቃላት መጽሐፍ ተመርቆ ለአንባቢያን በቃ - ኢዜአ አማርኛ
የጌዴኡፋ ቋንቋ የመዝገበ ቃላት መጽሐፍ ተመርቆ ለአንባቢያን በቃ
ዲላ ፤ጥቅምት 15/2016 (ኢዜአ) ፦በዲላ ዩኒቨርስቲ የተዘጋጀው የጌዴኡፋ ቋንቋ የመዝገበ ቃላት መጽሐፍ ተመርቆ ለአንባቢያን መብቃቱ ተገለጸ።
መጽሐፉ ከጌዴኡፋ ወደ አማርኛና እንግሊዝኛ የተተረጎሙ ከ4 ሺህ 200 በላይ ቃላት፣ ሐረጋትና አረፍተ ነገሮችን ያቀፈ ሲሆን በወረቀት ህትመትና በተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ የተዘጋጀ መሆኑም ተመላክቷል።
በዩኒቨርሲቲው የጌዴኡፋ ቋንቋና ስነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል ሃላፊና የመጽሐፉ ህትመት አስተባባሪና መምህር ዘነበ ሾቴ መጽሐፉ ሰዋሰውና የንግግር ቋንቋን ጨምሮ የተለያዩ የቋንቋ ዘውጎችን የያዘ ሲሆን ከ400 በላይ ገጾች እንዳሉት ጠቅሰዋል።
ለሰራ፣ ለጉብኝት፣ ለምርምርና ቋንቋውን መልመድ የሚፈልጉ ሰዎች ያለምንም አጋዥ ካሉበት ሆነው በተለያዩ አማራጮች ቋንቋውን መማር የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል።
ዩኒቨርሲቲው የጌዴኡፋ ቋንቋን ለማበልጸግ ከ500 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በመጀመሪያ ዲግሪ ከማሰልጠን ባለፈ የተለያዩ ምርምሮችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የጌዴኡፋ ቋንቋን ስነ ጽሑፍን ከማሳደግ ባለፈ ለመማሪያ ግብዓትነት ለመጠቀም የሚያስችል መጽሐፍ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
መጽሐፉ ከጌዴኡፋ ወደ አማርኛና እንግሊዝኛ የተተረጎሙ ከ4 ሺህ 200 በላይ አረፍተ ነገሮችን የያዘ መሆኑን ገልፀው በወረቀት ህትመትና በተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያነት መልክ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።
መፅሃፉ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን በአንድ ቋት የመሰነድ ፕሮጀክት አካል መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት ቡድን አባል ዶክተር ኬ ሼከር ናቸው።
ባለፉት ሶስት አመታትም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት ጌዴኡፋን ጨምሮ 12 የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን በመፅሐፍ ለተለያዩ መተግበሪያዎች አመች በሆነ መንገድ በድረ ገጽ እንዲሁም በድምጽ ጭምር መሰነድ መቻሉን አስረድተዋል።
ከነዚህም ቋንቋዎች አፋን ኦሮሞ፣ አማርኛ፣ ሲዳማአፎ፣ ሀዲይሳና ሌሎችንም ቋንቋዎች እንደሚያካትት ጠቅሰዋል።
''ይህም በምትችለው ቋንቋ የማትችለውን ቋንቋ መማርን ዓላማ ያደረገ'' መሆኑን ጠቅሰው ይህም የቋንቋ ብልጽግናና ብዝሃነትን ለማሳደግ ድርሻው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
የጌዴኦ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ ደርቤ ጅኖ በበኩላቸው መጽሃፉ በተለያዩ አማራጮች ለንባብ መብቃቱ የጌዴኡፋን ቋንቋ በቀላሉ በመማር የቋንቋውን ዕድገት ለማፋጠን ድርሻው የጎላ ነው ብለዋል።
በተለይ ዞኑ የይርጋጨፌ ልዩ ጣዕም ቡና መገኛና በዩኔስኮ የተመዘገበ ባህላዊ መልክዓ ምድር ባለቤት መሆኑን ተከትሎ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶችን የመሳብ አቅሙ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የዓለም አቀፍ ጎብኚዎችና ተመራማሪዎች ባሉበት ሆነው ስለ ቋንቋውና ባህሉ በቀላሉ እንዲረዱ የመጽሐፉ መታተም ድርሻው የጎላ ነው ብለዋል።
የዞኑ አስተዳደር የጌዴኡፋን ቋንቋና ባህል በማበልጸግ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም ከቋንቋ መማሪያ መጽሐፉ በተጨማሪ የጌዴኦ ታሪክ መጽሐፍ ህትመት እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።
የመፅሐፉ 950 ቅጅ የታተመ መሆኑና በቋንቋው ታሪክም ሁለተኛው የመዝገበ ቃላት ይዘት ያለው መጽሐፍ እንደሚያደርገው ተገልጿል።