ቀጥታ፡

 በየትኛውም ሁኔታ የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት መጠበቅ የሚያስችል ብቃትና ዝግጁነቱ አለን

 አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2016(ኢዜአ)፦ በየትኛውም ሁኔታ የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት መጠበቅ የሚያስችል ብቃትና ዝግጁነቱ አለን ሲሉ የአየር እና የባህር ሃይል አባላት ገለጹ።

116ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች በመስቀል አደባባይ በደማቅ ስነ ስርአት ተከብሯል።

በክብረ በዓሉ ላይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የተለያዩ አገራት የጦር አዛዦች፣ የጦር መኮንኖችና ሌሎችም እንግዶች ታድመዋል።

ከበአሉ ተሳታፊዎች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የአየር ሃይል እና የባህር ሃይል አመራርና አባላት በዓሉ ለሰራዊቱ ታላቅ ክብርና እውቅና በመስጠት በደማቅ ስነ-ስርአት በመከበሩ መደሰታቸውን ገልጸዋል።


 

ከአስተያየት ሰጭዎቹ መካከል ሻለቃ ሻምበል ዘገየ፤ የኢትዮጵያ አየር ሃይል በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ የላቀ ብቃት ባለው የሰው ሃይል የተሟላ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ አየር ሃይል ከየትኛውም ጊዜ በላቀ መልኩ የሀገርን የአየር ክልል የማስጠበቅ ቁመና ላይ ይገኛል ብለዋል።

በየትኛውም ሁኔታ የኢትዮጵያን የአየር ክልል መጠበቅ የሚያስችል ብቃትና ዝግጁነቱ አለን ሲሉ ተናግረዋል።


 

ሌላኛው አስተያየት ሰጭ ሀምሳ አለቃ አበበ ሀበሻ፤ አየር ሃይል የኢትዮጵያን ታላቅነት በሚመጥንና በዘመናዊ መልኩ ተገንብቷል ብለዋል።

በየትኛውም ሁኔታ ቢሆን የኢትዮጵያን የአየር ክልል ሉአላዊነት የማያስደፍር ብቁና ጀግና ሰራዊት መገንባቱን ገልጸዋል።


 

ሌላኛው የበዓሉ ተሳታፊ ሲንየር ዋረንት ኦፊሰር አለማየሁ ጥላሁን፤ ኢትዮጵያን ለመውረር በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች የመጡ ጠላቶችን በማሸነፍ ብዙ ጀግኖች ታሪክ ሰርተው ማለፋቸውን ጠቅሰዋል።

ለኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት መከበር እኛም በላቀ ዝግጁነት ላይ እንገኛለን ብለዋል።


 

ከኢትዮጵያ የባህር ሃይል አመራርና አባላት መካከል ሌፍተናንት ኮማንደር ቡሴሪ ቡልጉ፤ ከምንም በላይ ለሀገር ክብርና ሉአላዊነት የቆመ ሰራዊት መገንባቱን ገልጸዋል።

የባህር ሃይሉ በሁሉም አውድ አገርና መንግስት ለሚሰጠው ግዳጅ ሁሌም ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል። 


 

መርከቦቻችን ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን የሚያስችል ብቁ ቁመና አለን ያሉት ደግሞ ኤብል ሲ ማን ማለደ ጸጋዬ ናቸው።

የመከላከያ ሠራዊት ቀን "በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የፀና የድል ሠራዊት" በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም