መከላከያ ሠራዊታችን በግዳጅ አፈፃፀሙና በህዝባዊነቱ ህዝብና መንግስት የሚተማመኑበትና የሚኮሩበት ነዉ-አምባሳደር ሙክታር መሃመድ ዋሬ - ኢዜአ አማርኛ
መከላከያ ሠራዊታችን በግዳጅ አፈፃፀሙና በህዝባዊነቱ ህዝብና መንግስት የሚተማመኑበትና የሚኮሩበት ነዉ-አምባሳደር ሙክታር መሃመድ ዋሬ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 15/2016 (ኢዜአ) ፦ ሠራዊታችን በግዳጅ አፈፃፀሙና በህዝባዊነቱ ህዝብና መንግስት የሚተማመኑበትና የሚኮሩበት ነዉ ሲሉ በሱማሊያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሙክታር መሃመድ ዋሬ ተናገሩ።
የሴክተር 3 ሰላም አስከባሪ ሀይል "በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የሚፀና የድል ሠራዊት" በሚል መሪ ቃል እየተከበረ የሚገኘውን 116ኛዉ የሠራዊት ቀንን አክብረዋል።
በአከባበሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት በሱማሊያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሙክታር መሃመድ ዋሬ በደሙ ፍሳሽ በአጥንቱ ክስካሽና በእስትንፋሱ ህልፈት ኢትዮጵያን ከመጠበቅ ጀምሮ ለዓለም ሰላም መጠበቅ የሚከፍለዉን መስዋዕትነት መዘከር የውዴታ ግዴታችን ነዉ ብለዋል።
ሠራዊታችን በግዳጅ አፈፃፀሙና በህዝባዊነቱ ህዝብና መንግስት የሚተማመኑበትና የሚኮሩበት ነዉም ብለዋል በመልዕክታቸው።
አምባሳደሩ አክለውም የመከላከያ ሰራዊትን ስም የሚያጠለሹ የጥፋት ሀይሎች ከድርጊታቸዉ ሊቆጠቡ ይገባል ሲሉም አክለዋል።
የሴክተር ሶስት አዛዥ ብርጋዲየር ጀኔራል በስፋት ፈንቴ በበኩላቸዉ ሰራዊቱ ከምስረታው ጀምሮ የሀገርን ሉዓላዊ አንድነት እና ለዓለም ሰላም መረጋገጥ ዋጋ የከፈለ ህዝባዊ ሠራዊት ነው ብለዋል።
ይህን ዕለት የምናከብረዉ 7ኛ ዙር ለ8ኛ ዙር ሰላም አስከባሪ ሀይል ቀጠናውን ባስረከበበት ማግስት መሆኑ ልዩ ያደርገዋልም ሲሉም ገልጸዋል።
የሰው ልጅ ብዙ ነገር ይሰጣል የኢትዮጵያ ሰራዊት ግን ከደም ጠብታዉ እስከ መተኪያ የሌላት አንድ ህይወቱን የሚሰጥ መሆኑን አለም ቢያውቀውም እኛ የሱማሊያ ህዝብና መንግስት ግን ልዩ ምስክር ነን ያሉት ደግሞ በደቡብ ምዕራብ ሱማሊያ የባይደዋ ከተማ ከንቲባ አቶ አብዱላህ ዓሊ ናቸወ።
የኢትዮጵያ ሠራዊት የተረጋጋችና ጠንካራ መንግስት ያላት ሱማሊያን ለመገንባት በሚደረገዉ ርብርብ ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን የህዝባችንን ሰላም ለማረጋገጥ ልክ እንደ ሀገሩ በመቁጠር በጥሩ ስነ-ምግባር እንደሚጠብቅ የሱማሊያ ብሔራዊ ጦር የፀጥታ አመራሮች ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ሞቃድሾ የሚገኘዉ የአትሚስ ሰላም አስከባሪ ሀይል እና በሴክተሩ ስር የሚገኙት ሁሉም ሞተራይዝድ ሻለቆች በግዳጅ ቀጠናቸዉ የሠራዊት ቀንን ማክበራቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።