በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሻለቃ የሠራዊት ቀንን አከበረ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሻለቃ የሠራዊት ቀንን አከበረ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 15/2016 (ኢዜአ) ፦ የ17ኛ ሞተራይዝድ ሰላም አስከባሪ ሻለቃ በደቡብ ሱዳን በተሠማራበት የግዳጅ ቀጠና 116ኛውን የሠራዊት ቀን "በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የሚፀና የድል ሠራዊት" በሚል መሪ ቃል አክብሯል።
ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ጠንካራ ሰራዊት የነበራት፣ ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚነሱባትን ወራሪዎች በሠራዊቷ የጀግንነት ተጋድሎ እየመከተችና እያሸነፈች የመጣች ሀገር መሆኗን በክብረ በዓሉ ወቅት ተመላክቷል።
በዓለም አቀፍ ሠላም ማስከበር ረገድ እስከ አሁን በርካታ የሠራዊት አባላትን በማሰማራት ግዳጁን በድልና በጥሩ ዲስፒሊን እየፈጸመ እንደሚገኝ ተገልጾል ።
በአከባበር ሥነ ሥርዓቱ ንግግር ያደረጉት የሞተራይዝድ ሻለቃው አዛዥ ኮሎኔል ሞገስ ካሳዬ ኢትዮጵያ ልማቷንና እድገቷን ከማይፈልጉ የውጭ ወራሪዎች ራሷን አስከብራ የኖረችው ከጥንት ጀምሮ የተደራጀ፣ ጀግናና ፈተናዎችን በድል የሚሻገር ሠራዊት ስላላት መሆኑን አስገንዝበዋል።
ኮሎኔል ሞገስ “የአሁኑ ትውልዶች ከዘመኑ ጋር ዘምነን አኩሪ የጀግንነት ባህላችንን ማስጠበቅ ይገባናል” ሲሉም መናገራቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።