በደቡብ ወሎ ዞን የደረሰ ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ እየተሰበሰበ ነው

ደሴ ፤ ጥቅምት 15/2016(ኢዜአ)፡ -በደቡብ ወሎ ዞን የደረሰ ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ እየተሰበሰበ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማትና ጥበቃ ቡድን ባለሙያ አቶ ወንድይፍራው ጎቾ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በዞኑ በመኸር እርሻ 430 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለምቷል።

ከለማው መሬትም 13 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የገለጹት።

ሰሞኑን በአንዳንድ ወረዳዎች አልፎ አልፎ መጠነኛ ዝናብ እየጣለ መሆኑን ያመለከቱት ባለሙያው፣  የደረሱ ሰብሎች ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ሳይበላሹ ቀድሞ የመሰብሰብ ሥራ ከጥቅምት ወር መጀመሪያ ጀምሮ ተጠናክሮ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

እስካሁን በርብርብ በተከናወነ ሥራም ከ32 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ለምቶ ቀድሞ የደረሱ የገብስ፣ ቦለቄ፣ ማሾ፣ ጤፍ፣ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ምስርና ሌሎች ሰብሎችን ለመሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።


 

በሰብል መሰብሰብ ሥራው አመራሮችን ጨምሮ ባለሙያዎች፣ አርሶ አደሮችና በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውንም አቶ ወንድይፍራው አስረድተዋል።

አርሶ አደሩ የደረሰውን ሰብል ፈጥኖ ሲሰበስብ ዝናቡን በመፍራት ያልደረሰን ሰብል አብሮ በመሰብሰብ የምርት መቀነስና ብልሽት እንዳይከሰት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበትም አሳስበዋል።

"የደረሰን ሰብል ከመሰብሰብ ጎን ለጎን አርሶ አደሩ ቀሪ እርጥበት ለዳግም ሰብል ልማት መጠቀም አለበት" ያሉት አቶ ወንድይፍራው፣ የውሃ አማራጭ ባለበት አካባቢም ወደ በጋ መስኖ ልማት ፈጥኖ እንዲገባም አስገንዝበዋል፡፡

በቃሉ ወረዳ የቀበሌ 21 ነዋሪ አርሶ አደር ሰይድ አለሙ በሰጡት አስተያየት እንዳሉት በመኸር ወቅት አንድ ሄክታር ማሳ ላይ ያለሙት የማሾ፣ ቦለቄና ጤፍ ሰብል ቀድሞ በመድረሱ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ሳይበላሽ በመሰብሰብ ላይ ናቸው።

እስካሁን ከግማሽ የሚበልጠውን ሰብል መሰብሰባቸውን ጠቁመው፣ ከሰብሉም ከ20 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

"ሰሞኑን አልፎ አልፎ የሚያካፋው ዝናብ ቀድሞ በደረሰ ሰብል ላይ ጉዳት እንዳያስከትል በደቦ ጭምር ሰብል እየሰብሰብን ነው" ያሉት ደግሞ በአምባሰል ወረዳ የቀበሌ 04 ነዋሪ አርሶ አደር ኑርዬ ይማም ናቸው።

በደቡብ ወሎ ዞን ባለፈው ዓመት በመኸር እርሻ ከለማው 433 ሺህ ሄክታር ማሳ ከ11 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም