ቀጥታ፡

በኬሌ ከተማ ከ3 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር በላይ የኤሌክትሪክ መሥመር ማስፋፊያ ዝርጋታ ሥራ እየተካሄደ ነው---አገልግሎቱ

ኬሌ፤ ጥቅምት 15/2016 (ኢዜአ) ፡ - በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በኬሌ ከተማ ከ3 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር በላይ የውስጥ ለውስጥ የኤሌክትሪክ መሥመር ዝርጋታ እየተካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ ።

አዲስ በተደራጀው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዞኑ ከተደራጁት መካከል የቀድሞ አማሮ ልዩ ወረዳ መቀመጫ የሆነችው የኬሌ ከተማ ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲሟላላቸው ሲጠይቁ ቆይተዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአማሮ ኬሌ ደንበኞች አገልግሎት መስጫ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን ሙሐመድ ለኢዜአ እንዳስረዱት ተቋሙ የነዋሪዎችን ጥያቄ ታሳቢ በማድረግ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ነው።

በዚህም በበጀት ዓመቱ በከተማዋ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት 3 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር  የኤሌክትሪክ መስመር ማስፋፊያ ግንባታ ሥራ ማካሄድ ጀምሯል።

የመስመር ማስፋፊያ ዝርጋታው በከተማዋ ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነት አንጻር ከፍተኛ ቅሬታ ሲነሳባቸው የነበሩ መንደሮችን እንደሚያካትትም ተናግረዋል።

ለእዚህም በቀበሌ 02 የሁለት ኪሎ ሜትር መሥመር ዝርጋታ ሥራ በአሁኑ ወቅት መጀመሩን ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።


 

በከተማዋ ቀበሌ 01 የሚካሄደው ኤሌክትሪክ ሀይል ተሸካሚ መሥመር ዝርጋታ ደግሞ በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ለማስጀመር መታቀዱን ነው የገለጹት።

አቶ መስፍን እንዳሉት አዲስ የመስመር ዝርጋታ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ለመኖሪያ ቤት አገልግሎት የሚሰጡ ቆጣሪዎችና ኬብሎች ተዘጋጅተዋል።

አቶ ጳውሎስ ሙሐመድ የተባሉ የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲስተካከልላቸው ከ10 ዓመታት ላላነስ ጊዜ ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ተናግረዋል።


 

"የኤሌክትሪክ ሃይል ችግሬን ለመፍታት ከሌላ አካባቢ ደህንነቱ ባልተጠበቀና ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ የኤሌክትሪክ መስመር ስቤ ስጠቀም ቆይቼያለሁ" ብለዋል።

ወይዘሮ ዘብነሽ ብርሃኑ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ይጠቀሙበት የነበረው የኤሌክትሪክ መስመር ከነቤተሰባቸው ለስጋት ሲያጋልጣቸው መቆየቱን አስታውሰዋል።


 

በአሁኑ ወቅት ደረጃውን የጠበቀ የኤሌክትሪክ መስመር መዘርጋት መጀመሩ ይህን ችግራቸውን ስለሚያስቀር ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል። 

መምህር አርጋው ጥላሁን በሰጡት አስተያየት በከተማዋ ቀደም ሲል የተተከሉ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ደረጃቸውን ባለመጠበቃቸው እየወደቁ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በተደጋጋሚ ሲቆራረጥ እንደነበር ተናግረዋል።

በከተማዋ የአሌክትሪክ አገልግሎትን ለማቃለል በተጀመሩ ሥራዎች መደሰታቸውንም ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም