ቀጥታ፡

የመከላከያ ሰራዊት ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ የሚለው ሃሳብ የሚገለጽበት ታላቅ ብሔራዊ ተቋም ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 15/2016 (ኢዜአ) ፦የሀገር መከላከያ ሰራዊት ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ የሚለው ሃሳብ የሚገለጽበት ታላቅ ብሔራዊ ተቋም መሆኑን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

116ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን "በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የፀና የድል ሠራዊት" በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች በመላ ሀገሪቱ በመከበር ላይ ይገኛል።


 

በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የመከላከያ ኢታማዦር ሹሞች፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ ሚኒስትሮች፣ የፖሊስ አባላትና አመራሮች፣ ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተከብሯል።

በክብረ በዓሉ ላይ ንግግር ያደረጉት የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፤መከላከያ በአየር ኃይል፣ በምድር ኃይል፣ በባህር ኃይል እና በሳይበር እንዲደራጅ የተደረገበት ዋናው ዓላማ ትላንትና ዛሬና ነገን ለማስተሳሰር የሚያስፈልጉ አቅሞችን በተሟላ ቁመና ለማስቀጠል ነው ብለዋል። 

በመከላከያ ሰራዊት ላይ የተደረገው ጠንካራ የለውጥ ስራና አደረጃጀትም የተሰራበትና ከፍተኛ ውጤት የተገኘበት ለድል የሚያበቃ መሆኑን አንስተዋል። 

በኢትዮጵያ ታሪክ ከፍተኛ ቁጥርና ዘመናዊ ትጥቅ ያለው በልዩ ልዩ አገራት አስፈላጊ የሆኑ ወታደራዊ ታክቲኮችን የሰለጠነ የአመራር ብቃትን ያጎለበተ፣ ማቀድና ግዳጆችን በላቀ ብቃት መፈጸም የሚችል ሰራዊት ተገንብቷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከሀገር ባለፈ የአፍሪካ ኩራትና የብዙዎች የሰላም ማስከበር ተምሳሌት መሆኑንም ገልጸዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊቱ የተደራጀው በኢትዮጵያዊያን፤ የሚመራው በኢትዮጵያውያን የሚሰራውም ለኢትዮጵያ መሆኑን ጠቅሰው ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ የሚለው ሃሳብ የሚገለጽበት ታላቅ ብሔራዊ ተቋም ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም