የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ታላቅነት በሚመጥን መልኩ የተገነባና ለሀገር ክብርና ሉአላዊነት መከታ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ታላቅነት በሚመጥን መልኩ የተገነባና ለሀገር ክብርና ሉአላዊነት መከታ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 15/2016 (ኢዜአ)፦የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ታላቅነት በሚመጥን መልኩ የተገነባና ለሀገር ክብርና ሉአላዊነት መከታ መሆኑን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።
116ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን "በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የፀና የድል ሠራዊት" በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች በመስቀል አደባባይ በመከበር ላይ ይገኛል።
እለቱን ለማክበር ከተለያዩ አገራት የታደሙ የመከላከያ ኢታማዦር ሹሞች፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ ሚኒስትሮች፣ የፖሊስ አባላትና አመራሮች፣ ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው አንግዶች ተገኝተዋል።
በክብረ በዓሉ ላይ ንግግር ያደረጉት የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፤ የአገር መከላከያ ሰራዊት የአገር ጽናት ምልክትና ታሪካዊ መሰረት ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
ሰራዊቱ በታሪክ ላይ ቆሞ ኢትዮጵያን የማጽናት ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰው ዋነኛ አላማውም የኢትዮጵያን ሰላም በማጽናት ክብርና ሉአላዊነቷን ማስከበር ነው ብለዋል።
በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ባለፉት ጥቂት አመታት ሰፋፊ የሪፎርም ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በአስተሳሰብ ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰና አገሩን የሚወድ፣ በአደረጃጀት ሁሉን አቀፍና የተሟላ ቁመና እንዲኖረውና የመፈጸም አቅሙ ከፍ እንዲል ማሻሻያዎች መደረጋቸውንና በነዚህም ከፍተኛ ውጤት መገኘቱን አመልክተዋል።
በመሆኑም የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ታላቅነት በሚመጥን መልኩ የተገነባና ለሀገር ክብርና ሉአላዊነት መከታ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በመንግስታት ለውጥ ባልተለወጠ መንገድ አገርን አልፎም በተለያዩ አገራት በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ብቃቱን ያስመሰከረ ትውልድ ተሻጋሪ ሰራዊት መሆኑንም ገልጸዋል።
በተለያዩ ግዳጆች በተግባር ተፈትኖ የኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ ኩራትና የብዙዎች ምሳሌ መሆን ችሏል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
116ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን "በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የፀና የድል ሠራዊት" በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች በመላ ሀገሪቱ በመከበር ላይ ይገኛል።