ቀጥታ፡

በተግባር የተፈተነ የኢትዮጵያ የአፍሪካ ኩራት የብዙዎች ምሳሌ የሆነ የመከላከያ ሠራዊት መገንባት ተችሏል


አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 15/2016 (ኢዜአ)፦በተግባር የተፈተነ የኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ኩራት የብዙዎች ምሳሌ የሆነ የመከላከያ ሠራዊት መገንባት መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት 116ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን በመስቀል አደባባይ እየተከበረ ነው።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በአከባበር ስነስርአቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የመከላከያ ሠራዊት ኢትዮጵያን የሚመስል ጠንካራ ሃይል እንዲሆን ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሪፎርም ሰፋፊ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምን ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አስተሳሰብ ነጻ የሆነ የመከላከያ ሠራዊት መገንባት መቻሉን ገልጸዋል።

ከፍተኛ ቁጥር ያለው ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀና የሰለጠነ የአመራር ብቃትን  ያጎለበተ፣ በተግባር የተፈተነ የኢትዮጵያ፣ የምስራቅ አፍሪካ፣ የአፍሪካ ኩራት የብዙዎች ምሳሌ የሆነ የመከላከያ ሠራዊት ተገንብቷል ብለዋል።

የሰላም ምልክት የሆነው መከላከያ የልማት ምልክት ሆኖ እንዲቀጥልም የአስተሳሰብ፣ የአደረጃጀትና የማድረግ አቅም ላይ ሪፎርም መካሄዱን አስታውሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ኢትዮጵያ በማንም ሃይል ተሸንፋ እንደማታውቅና አሁንም እንደማትሸነፍ እንዲሁም ማንንም ሀገር ያልወረረችና አሁንም ማንንም እንደማትወርም ነው ያነሱት።

"በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የሚፀና የድል ሠራዊት " በሚል መሪ ቃል ነው 116ኛው  የሠራዊት ቀን በመላው ሀገሪቱ እየተከበረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም