የ116ኛው የሠራዊት ቀን በሀዋሳ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የ116ኛው የሠራዊት ቀን በሀዋሳ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው
ሀዋሳ ፤ጥቅምት 15 / 2016(ኢዜአ) ፡-116ኛው የሠራዊት ቀን በሀዋሳ ከተማ በተለያዩ መርሃ ግብሮች በድምቀት እየተከበረ ነው።
"በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የሚፀና የድል ሠራዊት” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ያለው የዘንድሮው 116ኛው የሠራዊት ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ የሠራዊቱን ጀግንነት በሚያወድሱ በተለያዩ መርሃ ግብሮች በመከበር ላይ ነው።
በሀዋሳ ከተማም በተመሳሳይ መርሃ ግብሩ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለሀገር ሉዓላዊነት በየጊዜው የከፈለውንና እየከፈለ ያለውን መስዋዕትነት በሚዘክሩ የተለያዩ መርሃ ግብሮች በመከበር ላይ ይገኛል።
በበዓሉ ላይ በሀገር መከላከያ ሠራዊት የደቡብ ዕዝ የሠራዊት አባላትና ከፍተኛ መኮንኖች ተገኝተዋል።
እንዲሁም የሲዳማ ክልልና የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሀይማኖት አባቶች ታድመዋል።
በአሁኑ ወቅት ከኢንዱስትሪ ፓርክ ጀምሮ በሀዋሳ ዋና ዋና መንገዶች የአገር መከላከያ ሠራዊትን የሚያወድሱ የተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
የሠራዊት አባላቱ በማርች ባንድ ጣዕመ ዜማ ታጅበው የመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ ወደሚከናወንበትና መልዕክት ወደሚተላለፍበት ቦታ በሰልፍ እያቀኑ ነው።
የበዓሉ ማጠቃለያ በሀዋሳ የቀድሞ ስታዲየም የተለያዩ መልዕክቶችን በማስተላለፍ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሚኒስቴር ደረጃ እንዲመራ ታስቦ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓጼ ሚኒልክ የጦር ሚኒስትር የተሾመው በ1900 ዓ.ም ሲሆን የመጀመሪያው ሚኒስቴርም ፊትአውራሪ ሀብተጊዮርጊስ መሆናቸውን ታሪክ ያወሳል።