ቀጥታ፡

ከቀደሙት ጀግኖች የተረከብናትን ሀገር ክብርና ሉአላዊነቷን በላቀ ብቃት ለማስከበር ዝግጁ ነን - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 15/2016 (ኢዜአ)፦ከቀደሙት ጀግኖች የተረከብናትን ሀገር ክብርና ሉአላዊነቷን በላቀ ብቃት ለማስከበር ከምን ጊዜውም በላይ ዝግጁ ነን ሲሉ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ። 

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት 116ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን በመስቀል አደባባይ እየተከበረ ነው።

እለቱን ለማክበር ከተለያዩ አገራት የታደሙ የመከላከያ ኢታማዦር ሹሞች፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ ሚኒስትሮች፣ የፖሊስ አባላትና አመራሮች፣ ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው አንግዶች ተገኝተዋል።

በክብረ በዓሉ ላይ ንግግር ያደረጉት የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ የሀገር መከታ የሆነው መከላከያ ሰራዊት ከምን ጊዜውም በላይ የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት ለማስከበር ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

እለቱ የሚከበረው የሀገር መከላከያ ሠራዊት በተቋም ደረጃ የተመሠረተበትን ጥቅምት 15 ቀን 1900 ዓ.ም መሰረት በማድረግ መሆኑን ገልጸው እለቱ ሲከበር በየጊዜው መስዋእትነት የከፈሉ ጀግኖችን ክብር በመስጠት ነው ብለዋል።

ከቀደሙት ጀግኖች የተረከብናትን ሀገር ክብርና ሉአላዊነቷን በላቀ ብቃት ለማስከበር ከምን ጊዜውም በላይ ዝግጁ ነን ሲሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ሉአላዊነት ተከብሮና አስተማማኝ ሰላም ሰፍኖ እንዲቀጥል ለማድረግ የሀገር መከታ የሆነው መከላከያ ሰራዊት ከምን ጊዜውም በላይ ዝግጁ ነው ብለዋል።

የውጭ ሃይሎች የኢትዮጵያን ሰላም ለማወክ የውስጥ ግጭት እንዲፈጠር የተለያዩ ሙከራዎችን እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው እነዚህ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ሰልጣን በሃይል ለመያዝ የሚደረግን የትኛውም ሙከራ ሀገር የማፍረስ እንቅስቃሴ በመሆኑ በፍፁም ተቀባይነት የሌለውና የማንታገሰው ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የሰራዊቱን ጀግንነትና ለሀገር የሚከፍለውን መስዋእትነት የሚያጣጥሉና ጥላሸት የሚቀቡ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል ብለዋል።

116ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን "በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የፀና የድል ሠራዊት" በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች በመከበር ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም