116ኛውን የመከላከያ ሠራዊት ቀን ስናከብር ኢትዮጵያ ለየትኛውም ሁኔታ ዝግጁ መሆኗን በማሳሰብ ነው -ሌተናል ጄነራል አለምሸት ደግፌ - ኢዜአ አማርኛ
116ኛውን የመከላከያ ሠራዊት ቀን ስናከብር ኢትዮጵያ ለየትኛውም ሁኔታ ዝግጁ መሆኗን በማሳሰብ ነው -ሌተናል ጄነራል አለምሸት ደግፌ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 15/2016 (ኢዜአ)፦ 116ኛውን የመከላከያ ሠራዊት ቀን ስናከብር ኢትዮጵያ ለየትኛውም ሁኔታ ዘወትር ዝግጁ መሆኗን በማሳሰብና በማመልከት ነው ሲሉ የጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪ እና የተኩስ አመራር ሃላፊ ሌተናል ጀነራል አለምሸት ደግፌ ገለጹ ።
"በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የፀና የድል ሠራዊት" በሚል መሪ ሀሳብ 116ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት በመስቀል አደባባይ በልዩ ልዩ ወታደራዊ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል።
በበአሉ ላይ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች፣ የተለያዩ ሀገራት ኤታማዦር ሹሞችና ፣ የክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች፣ ወታደራዊ አታሼዎች፣ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ የሠራዊቱ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
በዚህ ወቅት ንግግር ያደረጉት የጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪ እና የተኩስ አመራር ሃላፊ ሌተናል ጀነራል አለምሸት ደግፌ የኢትዮጵያ ሠራዊት ከአርበኞች ዘመን ጀምሮ ለሀገሩ ጽኑ ዋጋ ሲከፍል መኖሩን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሠራዊት ከኮርያ ዘመቻ እስከ ካራማራ ድል አኩሪ ታሪኩን በጀግንነት የፈጸመ መሆኑን አብራርተዋል።
116ኛውን የመከላከያ ሠራዊት ቀንንም ስናከብር የሠራዊቱን ታሪክና ተጋድሎ በማውሳት መሆኑን ተናግረው ሠራዊቱ በአሁኑ ወቅት የትኛውንም ጥቃት በብቃት ለመወጣት በአስተማማኝ ቁመና ላይ ይገኛል ብለዋል።
ሌተናል ጀነራል አለምሸት ደግፌ አክለውም ይህ በዓል ሲከበር ኢትዮጵያ ለየትኛውም ሁኔታ ዘወትር ዝግጁ መሆኗን በማሳሰብና በማመልከት ነው ሲሉ አስታውቀዋል።
በመርሐግብሩ የሠራዊቱን ታሪክ፣ ተጋድሎና ለመላው አፍሪካ ያበረከተውን ተምሳሌታዊ ገድል የሚያሳዩ መርሐ-ግብሮች እየቀረቡ ነው።
መከላከያ ሠራዊቱ አሁን የደረሰበትን አስተማማኝ ቁመና የሚያሳዩ ትርኢቶች እየቀረቡም ይገኛሉ።
ሠራዊቱ ለኢትዮጵያ ሉኣላዊነት የከፈለውን ዋጋ እና ታሪካዊ ጀግንነቱን የሚያወሱ ሁነቶችም ናቸው እየታዩ የሚገኙት ።
116ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን "በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የፀና የድል ሠራዊት" በሚል መሪ ሀሳብ በመላ ሀገሪቱ የሠራዊቱን ጀግንነት በሚያወሱ ሁነቶች እየተከበረ ነው።