ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ለአካባቢ ጥበቃ የሰጠችው ትኩረት የሚደነቅ ነው- በኢትዮጵያ የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ለአካባቢ ጥበቃ የሰጠችው ትኩረት የሚደነቅ ነው- በኢትዮጵያ የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለአካባቢ ጥበቃ የሰጠችው ትኩረት በምሳሌነት የሚጠቀስና የሚደነቅ መሆኑን በኢትዮጵያ የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ሚሮስላቭ ኮሴክ ገለጹ።
የቼክ ሪፐብሊክ የልማት ትብብር የአየር ንብረት ለውጥ መከላከልን በተመለከተ ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆነ ተቋማት ጋር በአዲስ አበባ ውይይት አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ሚሮስላቭ ኮሴክ፤ የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ፈተና ሆኖ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በተለይም በአፍሪካ ተጽዕኖው ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደሩ ለድርቅ፣ ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተትና ለሌሎች ተያያዥ ችግሮች ማጋለጡን አብራርተዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለአካባቢ ጥበቃ የሰጠችው ትኩረት በምሳሌነት የሚጠቀስና የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው ችግሩን ለመከላከልና ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት የአገራት ትብብር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሀገራትና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ የዓለም ልዩ ትኩረት ሆኖ ለጋራ መፈትሄ መስራት ይጠይቃል ብለዋል።
የዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዳንኤል ጎቦናያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የጋራ ምላሽ ይፈልጋል ብለዋል።
ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የሰጠችው ትኩረት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት አጋዥ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመድረኩ ቼክ ሪፐብሊክ በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ተጽዕኖ መቋቋም የሚያስችል የግብርና ልማት እንዲስፋፋና የአረንጓዴ ልማት እንዲጠናከር እየሰራች መሆኑ ተመላክቷል።