"ግሎባል ስታርትአፕ አዋርድ" ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ድጋፍ እንዲያገኙ ምቹ እድል ይፈጥራል - የስራና ክህሎት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
"ግሎባል ስታርትአፕ አዋርድ" ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ድጋፍ እንዲያገኙ ምቹ እድል ይፈጥራል - የስራና ክህሎት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2016(ኢዜአ)፦"ግሎባል ስታርትአፕ አዋርድ" በኢትዮጵያ ያሉ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ድጋፍ የሚያገኙበት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
የ2023 "ግሎባል ስታርትአፕ አዋርድ" የአፍሪካ ጉባዔ ዛሬ በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም ተጀምሯል።
በጉባኤው የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ እና ከተለያዩ የዓለም አገራት የመጡ ስራ ፈጣሪዎች ተገኝተዋል።
ጉባኤው ኢትዮጵያ በፈጠራ እና በቴክኖሎጂ ያላትን እምቅ አቅም ለማስተዋወቅ እና ሀገሪቱ በዘርፉ ያላትን ትክክለኛ ገጽታ ለማሳየት እንደሚያግዝ ሚኒስትር ሙፈሪያት ገልጸዋል።
በዓለም ላይ ለበርካታ ወጣቶች የስራ ዕድል እየፈጠረ ያለው "ግሎባል ስታርትአፕ አዋርድ" ኢኒሺዬቲቭ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች እየተጠቀሙ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በመድረኩ ከ30 የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ 15 ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች ለውድድር መታጨታቸውን ጠቁመው፤ በተቀመጠው ዓለም አቀፍ መስፈርት መሰረት አሸናፊው ይለያል ብለዋል።
በጉባኤው 300 መቶ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች እየተሳተፉ መሆናቸውን በመጠቆም።
ጉባኤው ስራ ፈጣሪዎችና የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች ከባለሃብቶች ጋር የሚያገናኝ መድረክ ነው ብለዋል።
ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች የሚያጋጥማቸውን ተግዳሮቶች በመለየት የመፍትሔ ሃሳብ ለማፍለቅና ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጠናከር ያግዛል ነው ያሉት ወይዘሮ ሙፈሪያት።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ ጉባኤው በማደግ ላይ የሚገኘውን የጀማሪ ስራ ፈጠራ ስነ- ምህዳር እንደሚያሳይ ገልጸዋል።
የአፍሪካ አገራት ለወጣት ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ፈጠራና ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ የወደፊት እድገት ውስጥ የማይናቅ ሚና እንዳላቸው በመገንዘብ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
የ2022 "ግሎባል ስታርትአፕ አዋርድ" አሸናፊ እና የኩቢክ ድርጅት መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ወጣት ቅዱስ ፍስሐ በበኩሉ በአፍሪካ በርካታ ወጣቶች የፈጠራ ሃሳብ እንዳላቸው ገልፆ መድረኩ ስራ ፈጣሪዎቹ ሃሳባቸውን እንዲያስተዋውቁ እድል እንደሚፈጥር ተገልጿል።
ዛሬ የተጀመረው የ2023 "ግሎባል ስታርትአፕ አዋርድ" የአፍሪካ ጉባኤ እስከ ጥቅምት 16/2016 ይቆያል።