የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከአትላንታ ከንቲባ ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከአትላንታ ከንቲባ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2016(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከአትላንታ ከተማ ከንቲባ አንድሬ ዲከንስ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም በሁለቱ ከተሞች በንግድ ፣ ኢንቨስትመንት ፣ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር ፣ በባህል እና በቱሪዝም መስኮች የተጀመሩ የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን ማጠናከር በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ መክረዋል።
የሁለቱ ከተሞች እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አትላንታ ቀጥታ በረራ ከጀመረ ወዲህ መጠናከሩን በዚህ ወቅት ገልጸው በዚህም ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ጎብኚዎች ቁጥር ከፍ ማለቱን ከንቲባዋ በውይይቱ ወቅት አንስተዋል፡፡
በቀጣይም የሁለቱን ከተሞች ትብብር ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እና ሌሎች የትብብር ዘርፎችን ለመለየት ከሁለቱም ከተሞች የተውጣጣ የቴክኒክ ቡድን በማቋቋም ለመስራት ከንቲባዎቹ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
በአትላንታ ቆይታቸው ለተሰጣቸው የክብር ዶክትሬት ፣ የጆርጂያ ዜግነት አዋርድ እንዲሁም በከንቲባ አንድሬ ዲከንስ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ከንቲባ አዳነች ምስጋና አቅርበዋል::
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአትላንታ ጆርጂያ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቅቀው ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውንም ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።