የፕሪሚየር ሊጉ አራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ መካሄድ ይጀምራሉ - ኢዜአ አማርኛ
የፕሪሚየር ሊጉ አራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ መካሄድ ይጀምራሉ
አዲስ አበባ ጥቅምት 14/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አራተኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ዛሬ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል።
ሻሸመኔ ከተማ ከሲዳማ ቡና ከቀኑ 9 ሰዓት ይጫወታሉ።
ዘንድሮ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ያደገው ሻሸመኔ ከተማ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች የተሸነፈ ሲሆን ተጋጣሚው ሲዳማ ቡና ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች በሁለቱ ተሸንፎ በአንዱ አቻ ተለያይቷል።
ሁለቱ ክለቦች በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ድላቸውን ለማስመዝገብ ይጫወታሉ።
በሌላኛው መርሐ ግብር ከምሽቱ 12 ሰዓት ድሬዳዋ ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ድሬዳዋ ከተማ እስከአሁን በሊጉ ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች አንዱን ሲያሸንፍ በአንዱ ተሸንፎ በቀሪው ጨዋታ አቻ ተለያይቷል።
ተጋጣሚው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ ካከናወናቸው ሶስት ጨዋታዎች በአንዱ በማሸነፍ በሁለቱ አቻ ወጥቷል።
የፕሪሚየር ሊጉ የአራተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል ሃዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ መድን ከቀኑ 9 ሰዓት፤ ወልቂጤ ከተማ ከባህር ዳር ከተማ ከምሽቱ 12 ሰዓት ይጫወታሉ።
የአራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች እስከ ጥቅምት 17/2016 የሚቆይ ይሆናል።