ቀጥታ፡

የመደመር እሳቤ ለሀገር ሀብት በመፍጠር እድገትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ትክክለኛ እይታ መሆኑ በተግባር እየተረጋገጠ ነው- ዶክተር ነመራ ገበየሁ 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2016(ኢዜአ)፦ የመደመር እሳቤ ለሀገር ሀብት በመፍጠር እድገትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ትክክለኛ እይታ መሆኑ በተግባር እየተረጋገጠ  መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ነመራ ገበየሁ ገለጹ። 

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እንደ ሀገር ከተገኙ ስኬቶች በመማር ከክልሉ አልፎ የሀገር ብልፅግና ለማረጋገጥ የሚያስችል ወሳኝ እንቅስቃሴ ላይ ነው ብለዋል። 

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በመተባበር “መደመር ሀብት ለመፍጠር፣ ፀጋን ለማስተዳደርና አርበኝነትን ለማሻገር” በሚል መሪ ሃሳብ ያዘጋጁት ሀገር አቀፍ የፓናል ውይይት በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል። 

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ነመራ ገበየሁ፤ “ሀብትና ብልፅግናን መፍጠር፣ ጸጋን ማስተዳደር በመደመር እሳቤ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አኳያ” የዳሰሰ የመወያያ ጽሑፍ አቅርበዋል። 


 

በመደመር እሳቤ ውስጥ የሰው ልጅ ከቁስ የዘለሉ በርካታ ፍላጎቶች እንዳለው በመገንዘብ፤ የለውጡ መንግስት ሁሉን አቀፍ ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

ሀገራዊ ትልሞችን ለማሳካትም በመደመር እሳቤ የጋራ ብልጽግና እና የወል እውነት ላይ ትኩረት ማድረጉን አብራርተዋል። 

ኢትዮጵያ የምታስበውን ሀብት ለመፍጠርና ብልጽግናን ለማረጋገጥም አምስት ጉዳዮች ላይ መተኮሩን ተናግረዋል። 

እነዚህም የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት፣ ከፍተኛ የቁጠባ ባህልና ኢንቨስትመት፣ ግልፅ የሆነ የልማት ፖሊሲ፣ የመንግስት የማስፈጸም አቅም፣ የኢኮኖሚ ብዝሃ ተሳታፊዎችን ያረጋገጠ ትብብርና ትስስር  ናቸው ብለዋል።

መደመር ሀብትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ አዳዲስ ዕይታዎችን ይዞ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ሀብት የሚፈጠረው በተደመረ ተሳትፎ፣ ኢኮኖሚው የብዝሃ ዘርፍ የእድገት ምንጭ እንዲኖረው በማድረግ መሆኑን ገልጸዋል። 

ሌላኛው ዕይታ ማከማቸትና ማካበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ ቀደም ሲሰሩ የነበሩ የልማት ስራዎችና የወጡ ፖሊሲዎችን ከዛሬ ትልሞች ጋር በማቀናጀት መስራት እንደሚገባ አዲስ መንገድ አምጥቷል ነው ያሉት። 

መደመር ኢትዮጵያ ያሏትን ጸጋዎች በመጠቀም ሀብትና ብልጽግና ለመፍጠር ትክክለኛ የኢኮኖሚ እድገት መነፅር መሆኑ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተጨባጭ ታይቷል ብለዋል። 

የተፈጥሮ ሀብትን መለየት፣ የሰው ሀብትን በአግባቡ ማወቅ፣ አብሮነትን ማጠናከር፣ የመሰረተ ልማት አቅም መፈተሽና ማሟላት ለጋራ ብልፅግና መሰረት መሆኑንም ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ተስፋ ሰጪ የሀብት መፍጠርና የብልጽግና ጉዞ ላይ መሆኗንም ጠቅሰዋል።  

የመንግስት ገቢ፣ የወጪ ንግድ እና የግብርና ምርታማነት ማደጋቸውን፣ የልማት ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜና በጀት በጥራት የማስፈጸም አቅም መሻሻሉንም እንዲሁ። 

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በርካታ ሀብት መፍጠርና ብልጽግናን ማረጋገጥ የሚያስችል እምቅ ሀብት እንዳለውም በጽሁፋቸው ዳስሰዋል። 

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እንደ ሀገር ጸጋዎችን በማልማት እየተመዘገቡ ካሉ ስኬቶች በመማር፣ ያለውን ህብረ ብሔር ስብጥር እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ጠንካራ ክልል መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። 

የህዝቡ የመዋቅራዊ አደረጃጀት ጥያቄ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ምላሽ ማግኘቱ ለቀጣይ ሁለንተናዊ የልማትና የብልጽግና ጉዞ ትልቅ አቅም መሆኑንም አብራርተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም