በምዕራብ ሸዋ ዞን የደረሰ ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ጉዳት እንዳይደርስበት እየተሰበሰበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ሸዋ ዞን የደረሰ ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ጉዳት እንዳይደርስበት እየተሰበሰበ ነው
አምቦ፤ (ኢዜአ) ጥቅምት 14/2016፡-በምዕራብ ሸዋ ዞን ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሰ ሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደረስ የመሰብሰብ ሥራ መጀመሩን የዞኑ እርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የዞኑ አርሶ አደሮች በበኩላቸው በደረሰ ሰብል ላይ ብክነትና ጉዳት ከመድረሱ በፊት በልማት ቡድናቸውና በቤተሰብ ተደራጅተው የደረሰ ሰብል እየሰበሰቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በጽህፈት ቤቱ የአዝዕርት ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ደጀኔ ገመቹ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በዞኑ እየጣለ ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሰ ሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያ መሣሪያዎችና በሰው ኃይል ምረት እየተሰበሰበ ነው።
በዞኑ በ2015/16 የምርት ዘመን በዘር ከተሸፈነው ማሳ ውስጥ እስካሁን ድረስ 39ሺህ 632 ሄክታር ስንዴ፣ በቆሎ፣ ጤፍና በሎቄ ወቅቱን ባልጠበቀው ዝናብ ጉዳት ሳይደርስበት ለመሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።
አርሶ አደሮች የደረሱ ሰብሎችን በደቦ፣ በዘመቻ እና ቤተሰቦቻቸውን በማሳተፍ እንዲያሰባስቡ ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም ቡድን መሪው አስታውቀዋል።
የግብርና ባለሙያዎች የደረሰው ሰብል በዝናብ ሳይበላሽ ታጭዶ እንዲከመርና በተሰበሰበበት ቦታ ሸራ በማልበስ ከብክነት ለመከላከል ከአርሶ አደሮች ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
የዞኑ አንዳንድ አርሶ አደሮች በበኩላቸው ወቅቱን ያልጠበቀው ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት ከማድረሱ በፊት በልማት ቡድናቸውና በቤተሰብ ተደራጅተው እየሰበሰቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የደንዲ ወረዳ አርሶ አደር መገርሳ ተረፈ በሰጡት አስተያየት በ2015/16 የምርት ዘመን ሙሉ የግብርና ፓኬጅ ተጠቅመው በጤፍ፣ ስንዴና ገብስ ካለሙት አንድ ሄክታር ማሳቸው ላይ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
ሆኖም አሁን እየጣለ ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በማሳው ላይ ጉዳት እንዳያስከትል ሰብላቸውን አጭደው የመከመር ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
"የደረሰ ሰብል በጊዜ እንድንሰበስብና ላልደረሰ ሰብል ተገቢውን ጥንቃቄ እንድናደርግ ግንዛቤ አግኝተን ወደሥራ ገብተናል" ያሉት ደግሞ የኤጀርሰለፎ ወረዳ አርሶ አደር ጥሩነህ ሁንዴሳ ናቸው።
አርሶ አደሩ እንዳሉት በግማሽ ሄክታር መሬት የዘሩት ስንዴ በመድረሱ ከጎረቤቶቻቸው ጋር በመተባበር ሰብሉን በመሰብሰብ እየከመሩ ነው።
የተከመረውን ሰብልም በዝናብ እንዳይበላሽ በላስቲክ መሸፈናቸውን ተናግረዋል።
በምዕራብ ሸዋ ዞን በተያዘው የመኸር ወቅት እየለማ ካለው 773 ሺህ ሄክታር መሬት ከ25 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የጽህፈት ቤቱ መረጃ ያመለክታል።