አብሮነትን መሰረት ያደረገ ዐቢይ ትርክት ለኢትዮጵያዊያን የጋራ እድገትና ህልውና ወሳኝ ሚና አለው-ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ - ኢዜአ አማርኛ
አብሮነትን መሰረት ያደረገ ዐቢይ ትርክት ለኢትዮጵያዊያን የጋራ እድገትና ህልውና ወሳኝ ሚና አለው-ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 14/2016 (ኢዜአ)፡- አብሮነትን መሰረት ያደረገ ዐቢይ ትርክት ለኢትዮጵያዊያን የጋራ እድገትና ህልውና ወሳኝ ሚና እንዳለው የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የኢዜአ ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ገለጹ።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በመተባበር “መደመር ሀብት ለመፍጠር፣ ፀጋን ለማስተዳደር እና አርበኝነትን ለማሻገር” በሚል መሪ ሃሳብ ያዘጋጁት ሀገር አቀፍ የፓናል ውይይት በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመደረኩ ላይ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የኢዜአ ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ የህዝቦች ትስስርና ዐቢይ ትርክት በሚል ርዕሰ የመወያያ ጽሑፍ አቅበዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ ከልዩነት ይልቅ ወንድማማችነትና ህብረ ብሔራዊ አንድነት የህልውናዋ መሰረት መሆኑን በመገንዘብ ተጨባጭ ውጤቶችን ያመጡ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በለውጡ ሂደት ውስጥ ክልሎች ያላቸውን ጸጋና እምቅ አቅምን አሟጦ መጠቀም የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ እንደፈተፈጠረላቸውም ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እምቅ ሀብትን ለመጠቀም፣ የህዝብን አቅም ተጠቅሞ የመልማት ትርክት መፍጠር አለበት ብለዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ትርክቶች መኖራቸውን ያነሱት ዶክተር ቢቂላ፣ አንደኛው “እኔ” ብቻ የሚል ከፋፋይ ንዑስ ትርክት በመሆኑ አይጠቅመንም ብለዋል።
ሁለተኛው የጋራ ፍላጎትና አብሮነትን መሰረት ያደረገው ዐቢይ ትርክት ነው፤ ለኢትዮጵያ የሚጠቅመውም ይህ ነው ብለዋል፡፡
ዐቢይ ትርክቱ የህዝቦች ትስስር፣ አንድነት፣ የጋራ ማንነት ላይ፣ “ችግርህ ችግሬ ነው” የሚል መተሳሰብን የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡
የወንድማማችነት፣ የአንድነትና አሰባሳቢ ትርክት ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልና ሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች የጋራ ህልውና ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝቦች ትስስር ተምሳሌት ነው ያሉት ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ፤ በውስጡ ያቀፋቸውን ብሔር ብሔረሰቦች የዘመናት አብሮነትን ለአብነት ጠቅሰዋል።
የህዝቦች ትስስር በየጊዜው የሚመጣና የሚሄድ ፖለቲከኛ የሚያፈርሰው ሳይሆን ስር የሰደደና ጠንካራ፣ በታሪክ፣ በቋንቋ፣ በጂኦግራፊያዊ፣ በባህልና አኗኗር የተጋመደ ነው ብለዋል።
በመሆኑም በቀጣይ የክልሉ አመራር የህዝቡን የጋራ ፍላጎቶች የሚያሳኩ ስራዎች ላይ ማተኮር፣ የህዝብን ትስስር ማጠናከርና ማስቀጠል፣ በዘላቂነት የህዝብን ጥቅም የሚያሟሉ ተቋማትን ማጠናከር፣ ንዑስ ትርክትን እንደመሳሪያ የሚጠቀሙ የፖለቲካ ነጋዴዎችን ማምከን ቀዳሚ ስራው አድርጎ እንዲንቀሳቀስ ጠይቀዋል።
የመደመር ጉዞ ምዕራፍ አምስት በሆነው የፓናል ውይይት ላይ የፌደራል መንግስትና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።