ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከናይጄሪያ አቻው ጋር ዛሬ ጨዋታውን ያደርጋል

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 13/2016 (ኢዜአ) ፦  በፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የአፍሪካ ዞን ሁለተኛ ዙር ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ከናይጄሪያ ጋር ዛሬ ታደርጋለች።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰዓት ከ 30 በአበበ በቂላ ስታዲየም ይካሄዳል።

በአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚሰለጥነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 25 ተጫዋቾችን በመያዝ ከጥቅምት 7/2016 አንስቶ በአዲስ አበባ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል።

ብሔራዊ ቡድኑ የመጨረሻ ልምምዱን ትናንት በ35 ሜዳ ማድረጉን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

በአንጻሩ በ67 ዓመቱ አሜሪካዊ ራንዲ ዋልድሩም የሚሰለጥነው የናይጄሪያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን 19 ተጫዋቾችን በመያዝ ዝግጅቱን ሲያደርግ የቆየ ሲሆን የመጨረሻ ልምምዱን ትናንት በአበበ በቂላ ስታዲየም አድርጓል።

አሰልጣኝ ራንዲ ዋልድሩም በአሜሪካ ባለባቸው የግል ጉዳዮች ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር በሚደረገው ጨዋታ ቡድናቸውን ሜዳ ተገኝተው እንደማይመሩ ተገልጿል።

ናይጄሪያዊ ረዳቶቻቸው ጀስቲን ማዱንጉ፣አን ቺዬጂኔና አዋል ማክዋላ ቡድኑን በዛሬው ጨዋታ እንደሚመሩ ተመላክቷል።

ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች የሴቶች እግር ኳስ ተሳትፎ አድርጋ አታውቅም፤ ተጋጣሚው የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ከዚህ ቀደም በውድድሩ ሶስት ጊዜ ተሳትፏል።

አልጄሪያዊቷ አትማን ላሚያ የሁለቱን ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመራሉ።

ሉሲዎቹ የመልስ ጨዋታቸውን ማክሰኞ ጥቅምት 20/2016 በአቡጃ የሚያደርጉ ይሆናል።

በኦሊምፒክ ሴቶች እግር ኳስ ማጣርያ የመጀመርያ ዙር ኢትዮጵያ ቻድን በድምር ውጤት 10 ለ 0 በማሸነፍ ወደ ሁለተኛው ዙር መሸጋገሯ የሚታወስ ነው።

በአራት ዙር በሚካሄደው የማጣሪያ ውድድር ሁለት አገራት አፍሪካን ወክለው በኦሊምፒክ ውድድሩ ላይ እንደሚሳተፉ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር(ፊፋ) አስታውቋል።

በሴቶች የእግር ኳስ ውድድሩ አዘጋጇ ፈረንሳይን ጨምሮ 12 አገራት እንደሚሳተፉ ገልጿል።

በፓሪስ በሚካሄደው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ28 የስፖርት አይነቶች ውድድሮች እንደሚከናወኑ የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አስታውቋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም