ቀጥታ፡

መደመር በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ያለውን እምቅ ሀብት፣ ባህልና ታሪክ ለሀገር ብልጽግና ለማዋል አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው- ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው 

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 14/2016 (ኢዜአ)፡- መደመር በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ያለውን እምቅ ሀብት፣ ባህልና ታሪክ ለሀገር ብልጽግና ለማዋል አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው ገለጹ። 

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በመተባበር “መደመር ሀብት ለመፍጠር፣ ፀጋን ለማስተዳደርና አርበኝነትን ለማሻገር” በሚል መሪ ሃሳብ ያዘጋጁት ሀገር አቀፍ የፓናል ውይይት በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው።  

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ክልሉ ከተመሰረተ ሁለት ወራት እንደሆነው ጠቅሰው፤ እስካሁንም በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል። 

አዲሱ ክልል በአረንጓዴ ልምላሜ የተሞላ፣ በርካታ የተማረ የሰው ኃይል ያለበት፣ ለንግድና ለምርምር ምቹ የሆነ አካባቢና እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ያለበት መሆኑን ገልጸዋል።

የመደመር ጉዞ መድረክ በክልሉ መዘጋጀቱም አካባቢውን ከማስተዋወቅ ባለፈ ህዝብን በአጀንዳዎች ዙሪያ በማሰባሰብ ለጋራ ብልጽግና እንዲሰራ የሚያነሳሳ መሆኑን ተናግረዋል። 


 

የመደመር እሳቤ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ያለውን እምቅ የተፈጥሪ ሀብት፣ የሰው ኃይል፣ ታሪክ፣ ባህልና ሀገር በቀል እውቀት በጋራ ጥረት መጠቀም የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመደመር እሳቤ የሀገራችንና የክልላችንን እቅዶች ለማሳካት ለሚደረገው ጥረት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው የዛሬው መድረክም ህዝቡን በጋራ ጉዳዮች ላይ ለማሰባሰብ ወሳኝ ነው ብልዋል። 

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ የመልማት አቅም ያለው በመሆኑ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና ለማረጋገጥ በጋራ እንስራ በማለት ጥሪ አቅርበዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፤ ኢዜአ የዛሬውን መድረክ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው አዲሱ ክልል በስራና ሀብት ፈጠራ፣ በህዝብ ትስስርና ባህል ያለውን ጸጋ ታሳቢ በማድረግ ለመደመር ሁነኛ ማሳያ በመሆኑ ነው ብለዋል።


 

በሁሉም ዘርፎች ስኬታማ ለመሆን እንደ ሀገር በሚደረግ የልማት አርበኝነት ክልሉ የራሱን አሻራ ለማሳረፍ የሚያስችል እምቅ ሃብት ያለው መሆኑንም ገልጸዋል። 

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከእዳ ወደ ምንዳ ለሚደረገው የሀገር ልማት እቅድ ስኬት አጋዥ የሚሆን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት፣ የሰው ኃይል፣ ባህልና በርካታ እሴቶችን የታደለ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም