የመከላከያ ሰራዊቱን ታላላቅ ታሪኮች በማስቀጠል ትውልዱ የራሱን ታሪክ መስራት አለበት - ኢዜአ አማርኛ
የመከላከያ ሰራዊቱን ታላላቅ ታሪኮች በማስቀጠል ትውልዱ የራሱን ታሪክ መስራት አለበት
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 14/2016 (ኢዜአ) ፦ የመከላከያ ሰራዊትን ታላላቅ ታሪኮችና ገድሎች አዲሱ ትውልድ በማስቀጠል የራሱን ታሪክ መስራት እንዳለበት ተገለጸ።
"በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የፀና የድል ሠራዊት" በሚል መሪ ሃሳብ 116ኛው የሠራዊት ቀን በነገው እለት በሀገር አቀፍ ደረጃ ይከበራል።
እለቱ እየተከበረ ያለው የሀገር መከላከያ ሠራዊት በዘመናዊ ደረጃ በተቋም የተመሠረተበትን ጥቅምት 15 ቀን 1900 ዓ.ም መሠረት በማድረግ ነው።
የበዓሉን አከባበር በማስመልከት የጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰ፤ በሰጡት መግለጫ በተደረገው ሪፎርም መሠረት ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የጦር ሚኒስትር በሠየመችበት ቀን የሰራዊት ቀን ሆኖ በደማቅ ሁኔታ መከበር ጀምሯል ብለዋል።
በመሆኑም ሀገራቸውን ከጠላት ለመፋለም መስዋዕት የሆኑ ጀግኖችን በመዘከርና ክብር በመስጠት በነገው እለት በተለያዩ መርሃ ግብሮች የሚከበር መሆኑን አብራርተዋል።
የሰራዊት ቀን መከበሩን በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ የቀድሞ ሰራዊት የድጋፍና የልማት ማሕበር ፕሬዚዳንት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ፤ የእለቱ መከበር ለሰራዊቱ ክብርና እውቅና ለትውልዱም ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ሰራዊት የላቀ ብቃት፣ ጀግንነትና ተልእኮ የመፈፀም ብቃት ትውልዱ በቅብብሎሽ እያወቀው የራሱን ታሪክ ለመፃፍ የሚዘጋጅበት መልካም አጋጣሚ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የሰራዊት ቀን በታላቅ ዝግጅት መከበር መጀመሩ የሰራዊቱን አኩሪ ገድልና የሰራቸውን ታሪኮች በትውልድ ቅብብሎሽ በቅጡ እየታወቀ እንዲዘልቅ የሚያደረግ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከሀገርም የሚሻገር ወርቃማ ታሪክ ያለው መሆኑን የገለጹት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ እየተሰጠው ያለው እውቅና ለሀገር የሚሰጥ ክብር መሆኑን ገልጸዋል።
የሰራዊቱን ታላላቅ ታሪኮችና ገድሎቹን ጠብቆ በማስቀጠል የአሁኑ ትውልድም የራሱን ታሪክ ለመስራት መዘጋጀት አለበት ብለዋል።
የሰራዊት ቀን ሲከበር መከላከያ ሰራዊት ሀገርንና ህዝብን የመጠበቅ ሃላፊነቱን በላቀ መልኩ ለመወጣት ዝግጁነቱን የሚያረጋግጥበት ይሆናል።