የአፍሪካ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች በወታደራዊ መስኩ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ትሥሥር ለማሳደግ እንደሚሩ ገለጹ

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 14/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ረጅም ዘመናት የካበተ የሠራዊት ግንባታ ያላት በመሆኑ ከሀገሪቱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማሳደግ እየሰሩ እንደሚገኝ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች ገለጹ።

116ኛውን የመከላከያ ሠራዊት ቀን አስመልክቶ የሠራዊቱን ታሪክ፣ ተጋድሎና አሁን የደረሰበትን አስተማማኝ ቁመና የሚያሳይ የፎቶ አውደ ርዕይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ለህዝባዊ እይታ ቀርቧል።

በመከላከያ ሚኒስቴር የወታደራዊ ታሪክ ቅርስ ጥናትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ተወካይ ኃላፊ ሌተናል ኮሎኔል አግዘው አልታየ አውደ ርዕዩ የሠራዊቱን የጀግንነት ታሪክና አሁን የደረሰበትን አስተማማኝ ቁመና የሚያመላክት ነው ብለዋል።

ሠራዊቱ ለኢትዮጵያ ሉኣላዊነት የከፈለውን ዋጋ እና ታሪካዊ ጀግንነቱን መዘከርም የአውደ ርእዩ ዋና አለማ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

የተዘጋጀውን አውደ ርእይ ለመታደም የመጡት የአፍሪካ ሀገራት ሚሊተሪ አታሼዎች አውደ ርእዩ የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት ታሪክ በጥልቀት እንድንረዳ ያስቻለን ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያና በአፍሪካ ሕብረት የዚምባቡዌ ሚሊተሪ አታሼ ብርጋዴር ጄኔራል ኢኔስ አሻሙ አውደ ርእዩ ስለ ኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ታሪክ የነበራቸውን ግንዛቤ የሚያሳደግ ሆኖ እንዳገኙት አብራርተዋል።


 

ኢትዮጵያና ዚምባቡዌ በወታደራዊ መስኩ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው አንስተው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የዘርፉን ግንኙነት የሚያጠናክሩ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የጋቦን ሚሊተሪ አታሼ ኃላፊ ኮሎኔል አርስቲዴ አንጉሌት በበኩላቸው አውደ ርእዩ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የገዘፈ ታሪክ ባለቤት መሆኑና የሠራዊቱን ሁለገብ እድገት የታየበት ስለ መሆኑ አብራርተዋል።


 

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ያለው እምቅ አቅም ለአፍሪካ ሀገራትም ምሳሌ መሆኑን አውስተው ጋቦን እና ኢትዮጵያ በወታደራዊ ዘርፉ ያላቸውን ትስስር ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እንደሚከናወን አብራርተዋል።

116ኛውን የመከላከያ ሰራዊት ቀን አስመልክቶ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር የተዘጋጀውን የፎቶ አውደ ርዕይ አርበኞች፣ የቀድሞ የሰራዊት አባላት እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየጎበኙት ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም