ቀጥታ፡

የአገር መከላከያ ሰራዊትን ማክበር ኢትዮጵያን ማክበር ነው - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 13/2016 (ኢዜአ) ፦ የአገር መከላከያ ሰራዊትን ማክበር ኢትዮጵያን ማክበር ነው ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።

ለአገር መከላከያ ሰራዊት በተለያዩ መስኮች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የክብር አባልነት እውቅና ተሰጥቷል።

116ኛው የሰራዊት ቀን "በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የሚጸና የድል ሰራዊት" በሚል መሪ ኃሳብ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ነው።
 
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ለጋዜጠኞችና በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ማኅበረሰቡን በማንቃት ለተሳተፉ አካላት እውቅናውን ሰጥተዋል።
 



የሰራዊቱ የክብር አባል ማድረጊያ በአዋጅ ተደንግጎ የተቀመጠ መሆኑንና በመመሪያው መሰረት ለመጀመሪያ ጊዜ የተከናወነ መሆኑም ተገልጿል።
 
እውቅና የተሰጣቸው ግለሰቦች በሰራዊቱ ላይ የሚሰነዘሩ የማኅበራዊ ሚዲያ ጥቃቶችን ሲከላከሉና ሲጋፈጡ እንዲሁም ሲመክቱ የነበሩ መሆናቸው ተመላክቷል።
 
የጠላት ሴራ እንዳይሳካ ሌት ተቀን ከሰራዊቱ ጋር ሲሰሩ የነበሩ መሆናቸውም ተጠቅሷል።   

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ ይህንን እውቅና ያገኙ አካላት ሰራዊቱን አክብረው ላከናወኑት ሥራ ምስጋና አቅርበዋል።
 
በሥራቸውም የሰራዊቱን መልካም ሥነ-ምግባር እንዲሁም ዝና በማስገንዘብ ስሙን ለማጠልሸት ከሚሯሯጡ የጠላት አካላት ታድገዋል ብለዋል።

በቀጣይም በተመሳሳይ ተግባራት ላይ ለሚሳተፉ አካላት ይህ እውቅና እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
የመከላከያ ሰራዊት ማለት አገር ማለት ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የአገር መከላከያ ሰራዊትን ማክበር ኢትዮጵያን ማክበር ነው ብለዋል።  
 
ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ያሉበት ትንሿ ኢትዮጵያ መሆኑንና የአገር አደራ የተረከበ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የመጨረሻ ምሽግ ነው ሲሉም ገልጸዋል። 
 
ሰራዊቱ አገርን ሉዓላዊነትን እንዲሁም በሕገ-መንግሥት በተሰጠው ሥልጣን መሰረትም ሰላምን የማስከበር ሥራዎችን እንደሚያከናውን ተናግረዋል። 

ይህንን የሚሰራ አካል ከሌለ አገር አለማለት እንደማይቻልም ነው የገለጹት። 

እውቅና የተሰጣቸውም ግለሰቦች የተሰጣቸው ክብር እንዳስደሰታቸው ገልጸው በየትኛውም አካባቢ ለሰራዊቱ ክብር መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያን መከላከያ ውስጥ ማየት እንደሚቻል ጠቁመው በቀጣይም መሰል ተግባራትን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል። 

በመርኃ ግብሩ የሰራዊቱ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች እንዲሁም ሚኒስትሮች ታድመዋል።
 
በ116ኛው የሰራዊት ቀን ለመታደም የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ወታደራዊ መሪዎች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ መሆኑ ይታወቃል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም