የኮንስትራክሽን ዘርፉ ለአገራዊ እድገት የሚጠበቅበትን ድርሻ እንዲወጣ በትኩረት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኮንስትራክሽን ዘርፉ ለአገራዊ እድገት የሚጠበቅበትን ድርሻ እንዲወጣ በትኩረት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 13/2016 (ኢዜአ)፦ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ለአገራዊ እድገት የሚጠበቅበትን ድርሻ እንዲወጣ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ገለጸ።
በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲቱዩት እና በኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ማህበር ትብብር የተደረገውን ጥናት መነሻ በማድረግ የኮንስትራክሽን ዘርፉን ለማነቃቃት የሚያግዝ የተለያዩ አካላት የተገኙበት ውይይት ተደርጓል።
በመድረኩም ዓለም አቀፍና ሀገራዊ ሁኔታዎች በኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደሩ መሆኑ ተነስቷል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴዔታ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ፤ የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ እድገትና መሻሻል ቢኖረውም የተለያዩ ችግሮች እያጋጠሙት መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ችግሮችን በሂደት በመፍታት ዘርፉ ለአገራዊ እድገት የሚጠበቅበትን ድርሻ እንዲወጣ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለኮንስትራክሽን ዘርፉ መነቃቃት የሚያግዙ የመፍትሔ እርምጃዎች በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥሉ መሆኑንም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ ማህበር ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ኤርሚያስ እንግዳ፤ ባቀረቡት ጽሁፍ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ላይ ከግብርና በመቀጠል ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል ብለዋል።
የዓለም አቀፍ ወቅታዊ ሁኔታ፣ በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ጸጥታ ችግሮች፣ በዘርፉ ላይ የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት፣ ሙስና፣ ቢሮክራሲ መብዛትና የግብዓት እጥረት ለዘርፉ ማነቆ መሆናቸውን አንስተዋል።
ዘርፉ ለምጣኔ ሃብታዊ እድገት ላይ ሊያበረክት የሚገባውን ድርሻ እንዲወጣ መንግስት ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር በቅርበት መስራት እንዳለበት መክረዋል።
የኮንስትርክሽን ማኔጅመነት ኢንስቲቱዩት ዳይሬክተር ኢንጅነር ታምራት ሙሉ፤ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ የሚስተዋለውን የባለሙያ እጥረት ለማቃለል ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
የውይይት መድረኩ "የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ፣ የስራ እድልና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ" በሚል መሪ ሃሳብ ነው የተካሄደው።