የመንግስታቱ ድርጅት እየተለወጠ ያለውን የዓለም ሁኔታ ያማከለ ፍትሐዊ ተቋማዊ ማሻሻያ ማድረግ ይኖርበታል - አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስታቱ ድርጅት እየተለወጠ ያለውን የዓለም ሁኔታ ያማከለ ፍትሐዊ ተቋማዊ ማሻሻያ ማድረግ ይኖርበታል - አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 13/2016 (ኢዜአ)፦ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በፍጥነት እየተለወጠ ከሚገኘው የዓለም ሁኔታ ጋር የሚራመድ ሁሉን አቃፊና ፍትሐዊ ተቋማዊ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚገባው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።
ማሻሻያው አፍሪካን ጨምሮ ሌሎች በማደግ ላይ የሚገኙ አገራትን ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበትም ብለዋል።
የ2023 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቀን "የአየር ንብረት ለውጥ እርምጃ አውደ ግንባሮች" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዛሬ ተከብሯል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ፣ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት የስራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ኢትዮጵያ የተመድ መስራች አባል አገርና ከድርጅቱ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጋር ስድስት አስርት ዓመታትን ያስቆጠረ ፍሬያማ የትብብር ታሪክ እንዳላት አምባሳደር ምስጋኑ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ኮሚሽኑ ዋና መቀመጫው አዲስ አበባ እንዲሆን በተደረገበት ታሪካዊ ውሳኔ የነበራት አስተዋጽኦ የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ከማስተዋወቅ አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን አመልክተዋል።
ዓለም በአሁኑ ሰዓት በፈጣን ሁኔታ ለውጦችን እያስተናገደች እንደምትገኝና ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲውም በተለዋዋጭ ሁኔታዎች እያለፈ ይገኛል ብለዋል።
ተመድ የዓለምን አሁናዊ ነባራዊ እውነታ ከግምት ውስጥ ያስገባ ፍትሐዊና ሁሉን አሳታፊ ተቋማዊ ማሻሻያ በማድረግ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንዳለበት ነው አምባሳደር ምስጋኑ የገለጹት።
ድርጅቱ በባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ስራው የአፍሪካና በማደግ ላይ የሚገኙ አገራትን ፍላጎትና ድምጽ ማካተት እንደሚኖርበትም አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ስርዓት መጎልበት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
ተመድ ኢትዮጵያ እየተገበረች ላለችው የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድና በአገሪቱ እየተከናወኑ ላሉ የልማት ስራዎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል አምባሳደሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ-መንበር ዶክተር ሞኒክ ንሳንዛባጋንዋ፤ በአህጉሪቱና በተለያዩ ዓለማት የሚከሰቱ ፈተናዎችን ምላሽ ለመስጠት በትብብር መስራት ይጠይቃል ብለዋል።
የስርዓተ ጾታ እኩልነት፣ ነፃነትና ፍትሕዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የኢኮኖሚ ሥርዓት መገንባት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
የአፍሪካን ቀጣይነት ያለው ደህንነትና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስቀጠል ለፈጠራ ስራዎች ትኩረት መስጠት ይኖርብናልን ነው ያሉት።
የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተጠባባቂ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ፔድሮ፤ ዘላቂ ሰላምና ልማትን በማረጋገጥ ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የተመድ ቻርተር ዲፕሎማሲያዊ ትብብርን ለማስፋት የሚያስችሉ መርሆዎችን መያዙን ጠቅሰው የትብብር እድሎችን በማስፋት ለሴቶች ተጠቃሚነት መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቀን ድርጅቱ እ.አ.አ 1971 ባሳለፈው የውሳኔ ሀሳብ ቁጥር 2782 አማካኝነት በየዓመቱ በተመድ አባል አገራት እየተከበረ ይገኛል።
ቀኑ እ.አ.አ የተቋቋመውን 1945 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምስረታ በማሰብ የሚከበር ነው።