ቀጥታ፡

መከላከያ ሰራዊት ሀገር ለማጽናት እየከፈለ ላለው መስዕዋትነት ተገቢውን ክብርና እውቅና መስጠት ይገባል

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 13/2016 (ኢዜአ) ፡-  መከላከያ ሰራዊት ሀገር ለማጽናት እየከፈለ ላለው መስዕዋትነት ተገቢውን ክብርና እውቅና መስጠት እንደሚገባ ተገለጸ።

የ116ኛ የሰራዊት ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡  

በመድረኩ ላይም ሰራዊቱ ኢትዮጵያ በተፈተነችበት ጊዜ ፈተናዎችን በድል እየተሻገረ አኩሪ ገድል የፈጸመ እና በመፈጸም ላይ የሚገኝ የሀገር ባለውለታ መሆኑ ተገልጿል።  

የጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪ እና የተኩስ አመራር ሃላፊ ሌተናል ጀነራል አለምሸት ደግፌ፤ የመከላከያ ሰራዊቱን ቀን መዘከር የተፈለገው ሰላምን ማክበርና ማጽናት ስለሚገባ ነው ብለዋል፡፡

የአገሩን ሰላም ለማጽናት የህይወት ዋጋ እየከፈለ ላለ ሰራዊት ተገቢውን እውቅና እና ክብር መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት።   

የሰራዊቱ ተጋድሎ አጭር ታሪክ ያለው አይደለም ያሉት ሌተናል ጀነራሉ አሁንም በድል ታጅቦ እየቀጠለ ይገኛል ብለዋል፡፡

በየትኛውም ተልእኮና ግዳጅ በጀግንነቱ፣ ሀገርና ህዝብ ወዳድነቱና ሰላም አስከባሪነቱ የላቀ ስም ያለውን መከላከያ ሰራዊት እውቅና መስጠት ተገቢ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የሰራዊቱን የተጋድሎ፣ የጀግንነትና የመስዋእትነት እውነታዎች ለማጣጣል የሚጥሩ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል በማለት አሳስበዋል።

        

የቀድሞ ሰራዊት አባል ጀነራል ተስፋዬ ሃብተማርያም፤ የኢትዮጵያ ሰራዊት ተናንትም ይሁን ዛሬም የአገሩን ዳር ድንበር በማስጠበቅ ረገድ አኩሪ ተጋድሎ የፈጸመ እና እየፈጸመ ያለ ጀግና ሰራዊት ነው ብለዋል፡፡   

    በመድረኩ የመከላከያ ሰራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖች፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ተወካዮች፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት አመራሮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። 

116ኛው የሠራዊት ቀንን በማስመልከት የተለያዩ መርሃ-ግብሮች እየተከናወነ ሲሆን ቀኑ "በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የፀና የድል ሠራዊት" በሚል መሪ ሃሳብ ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከበር ይሆናል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም