በኢትዮጵያ የእንስሳት መኖ አቅርቦትና ጥራትን ለማሻሻል የሚያስችል መርሐ ግብር ይፋ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የእንስሳት መኖ አቅርቦትና ጥራትን ለማሻሻል የሚያስችል መርሐ ግብር ይፋ ተደረገ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 13/2016 (ኢዜአ) ፡- በኢትዮጵያ የእንስሳት መኖ አቅርቦትና ጥራትን በማሻሻል የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብሩን ስኬታማ ማድረግ የሚያስችል መርሐ ግብር ይፋ ተደረገ፡፡
የግብርና ሚኒስቴር ከላንድ ኦ ሌክስ ቬንቸር 37 ጋር በመተባበር ይፋ ያደረጉት መርሐ ግብር የእንስሳት መኖን ለገበያ በሚመጥን ጥራትና መጠን ማቅረብ የሚያስችልና ለአምስት ዓመታት የሚቆይ ነው ተብሏል፡፡
የዛሬው መርሐ ግብር በኢትዮጵያና ኬንያ ያለውን የእንስሳት ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ታልሞ የተዘጋጀ መሆኑም ተገልጿል።
በኢትዮጵያ የእንስሳት መኖ አቅርቦትን በማሻሻል የወተት ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሲዳማ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ አትዮጵያና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ገቢራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ እንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አስራት ጤራ እንዳሉት፤ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የተያዙ እቅዶችን ለማሳካት የእንስሳትን ዝርያ ማሻሻልና ምርታማነትን ማሳደግ ወሳኝ ነው፡፡
በኢትዮጵያ በክረምት ከፍተኛ የሆነ መጠን ያለው የእንስሳት መኖ የሚገኝ ቢሆንም በአግባቡ ስለማይሰበሰብ በበጋ ወቅት እጥረት እንዲከሰት ያደርጋል ነው ያሉት ።
በመሆኑም በክረምት በብዛት የሚመረተውን የእንስሳት መኖ በበጋ ወቅት ጭምር አገልግሎት እንዲሰጥ አርሶ አደሩን በእውቀት፣ በቴክኖሎጂና አሰራር መደገፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ የሌማት ትሩፋትና የስንዴ ልማት ፕሮግራም የእንስሳትን መኖ አቅርቦት በማሻሻል ሚናቸው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በበጋ መስኖ ከስንዴ የሚገኘውን ተረፈ ምርት አያያዝና አጠቃቀም ማሻሻል፤ የምጥን መኖ አጠቃቀም ልምድን ማሳደግ እና የገበያ ትስስር መፍጠር ቅድሚያ ሰጥተን የምንሰራበት ነው ብለዋል፡፡
በዛሬው ዕለት ይፋ የሆነው መርሃ ግብርም ኢትዮጵያ ቀድማ የጀመረችውን የዜጎችን የምግብ ሉዓላዊነት የማረጋገጥ ሂደት አጋዥ መሳሪያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በላንድ ኦ ሌክስ ቬንቸር 37 የቴክኒክ እና ኢኖቬሽን ቡድን ዳይሬክተር ዳይ ሀርቬይ በኢትዮጵያ ከ 70 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ የእንስሳት ሀብት ባለቤት መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
በመሆኑም በምስራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያና ኬንያ ገቢራዊ በሚሆነው በዚህ መርሃ ግብር ከ100 ሺህ በላይ የወተት አምራቾች ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል፡፡
ይሄውም የሀገሪቱን 40 በመቶ ድርሻ የሚይዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ 40 በመቶ የሚሆነው የድርቆሽ መኖ ያለ አግባብ እንደሚባክን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ የመርሃ ግብሩ ዓላማ በምሥራቅ አፍሪካ የእንስሳትን አመጋገብ በማሻሻል ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡