ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በተመድና በአፍሪካ መካከል ያለውን አጋርነት ለማጠናከር ትሰራለች

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 13/2016 (ኢዜአ) ፡- ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታትና በአፍሪካ መካከል ያለውን አጋርነት ለማጠናከር እንደምትሰራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።

78ኛው የተባበሩት መንግስታት ቀን የተመድ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች እና የአፍሪካ ህብረት ተወካዮች በተገኙበት በድርጅቱ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ተከብሯል።

አምባሳደር ምስጋኑ በመርኃ-ግብሩ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በአፍሪካ እና በተመድ መካከል ያለውን አጋርነት ለማጠናከር እንደምትሰራ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በድርጅቱ ስርዓት ውስጥ ለሚስተናገዱ የባለ ብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ድምጾች ያላትን አክብሮት ገልጸው ድርጅቱ አሁን ያለውን የዓለም ስርዓት ያገናዘበ ሪፎርም እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።


 

ኢትዮጵያ ከተመድ መስራች ሀገራት መካከል አንዷ እንደ መሆኗ የድርጅቱን መርሆዎች እንደምታከብር አክለዋል።

ከተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጋር ያለውን አጋርነት ለማጠናከርና ኮሚሽኑን ለማገዝ ቁርጠኛ መሆኗንም አምባሳደር ምስጋኑ ገልጸዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ አክለውም ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ለተመድ ቻርተር ያላውን ቁርጠኝነት እንዲያድስ ጥሪ ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም