ቀጥታ፡

“መደመር ሀብት ለመፍጠር፣ ፀጋን ለማስተዳደር አርበኝነትን ለማሻገር” በሚል መሪ ሀሳብ የፓናል ውይይት በሆሳዕና ከተማ ይካሔዳል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ጋር በመተባበር “መደመር ሀብት ለመፍጠር፣ ፀጋን ለማስተዳደር አርበኝነትን ለማሻገር” በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው የፓናል ውይይት በሆሳዕና ከተማ ነገ ይካሔዳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከትላንት በመማር፣ ዛሬን በማላቅ ለነገ መንገድ የሚጠቁም በሀገር በቀል ዕውቀት ላይ የታነጸ የመደመር እሳቤን ለሀገር ማበርከታቸው ይታወቃል።

እሳቤው በሚገባ እንዲሰርጽና ለትውልድ እንዲተላለፍም “መደመር”፣ “የመደመር መንገድ” እና “የመደመር ትውልድ“ የሚሉ መጽሃፍትን ለንባብ አብቅተዋል።

ኢዜአም “የመደመር ጉዞ” በሚል ማዕቀፍ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፉ የፓናል ውይይት መድረኮችን በተለያዩ የሃገራችን ከተሞች እያካሄደ ይገኛል።

የመድረኮቹ ዋነኛ ዓላማም በመደመር እሳቤ ላይ ሰፊ ግንዛቤ በመፍጠር ብሄራዊ መግባባት፣ አንድነትና አብሮነትን ማጠናከር ነው።

በነገው ዕለትም “መደመር ሀብትን ለመፍጠር፣ ፀጋን ለማስተዳደር፣ አርበኝነትን ለማሻገር” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው የፓናል ውይይት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ይካሄዳል::

በመድረኩም መደመርና የአዲሱ ትርክት ብሄራዊ ፋይዳ፣ ሀብትን መፍጠርና ፀጋን ማስተዳደር በመደመር እንዲሁም የአመራር የስራ ባህል ብልፅግናን ለማረጋገጥ የሚሉ የውይይት መነሻ ጽሁፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በመድረኩ ላይም የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ አመራሮች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና ሌሎችም እንግዶች ተሳታፊ ይሆናሉ።

ከዚህ ቀደም የመደመር ጉዞ የፓናል ውይይት መድረኮች በአዲስ አበባ፣ ቢሾፍቱ፣ ጅግጅጋና አሶሳ ከተሞች የተካሄዱ ሲሆን፤ በነገው እለት የሚካሂደው መድረክም ምዕራፍ አምስት መሆኑ ተገልጿል።

የምዕራፍ አራት መድረክ “መደመር ለጠንካራ አገረ መንግስት ግንባታና ህብረ-ብሄራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ ባሳለፍነው መስከረም ወር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ መካሄዱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም