የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት የ10 ነጥብ 5 በመቶ እድገት እንዲያስመዘግብ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት የ10 ነጥብ 5 በመቶ እድገት እንዲያስመዘግብ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 13/2016 (ኢዜአ) ፦ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት የ10 ነጥብ 5 በመቶ እድገት እንዲያስመዘግብ እየተሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ለአገራዊ የምርት እድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
ለተያዘው እቅድ ስኬትም ኢንዱስትሪዎችን የማስፋፋት፣ ምርታማነታቸውን የማሳደግና አዳዲስ ኢንቨስትመንትን የማምጣት ስራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።
በዘርፉ የግብአትና የፋይናንስ ቅርቦትን የማሳለጥ ስራ እንደሚከናወን ጠቅሰው በተያዘው ዓመት ብቻ በዘርፉ 327 ሺህ አዲስ የስራ እድል ለመፍጠር መታቀዱን ጠቅሰው የግብአትና የፋይናንስ አቅርቦትም የሚመቻች መሆኑን ገልጸዋል።
በዘንድሮው ዓመት በመንግስት በኩል ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን የገለጹት ሚኒስትር ዴታው በተለይም የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ለመደገፍ የፖሊሲ ማሻሻያ መደረጉን አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የኮርፖሬት ኢንዲስትሪ ፋይናሲንግ ተጠባባቂ ምክትል ፕሬዚዳንት አዳነ መሃሪ፤ ለአምራች ኢንዱስትሪው ባንኩ የብድር አገልገሎት ማመቻቸቱን ገልጸዋል።
የብድሩ ተጠቃሚዎች ቅድመ ሁኔታዎችን በማሟላት ወደ ስራ እንዲገቡ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።
በተያዘው ዓመት ባንኩ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች 51 ቢሊዮን ብር ብድር ለመስጠት መዘጋጀቱ ታውቋል።