ቀጥታ፡

ኮሚሸነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በቻይና የህዝብ ደህንነት ምክትል ሚኒስትር ዡ ዳቶንግ የተመራ ልዑክን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 13/2016 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሸነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በቻይና የህዝብ ደህንነት ምክትል ሚኒስትር ዡ ዳቶንግ የተመራ ልዑክን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።

የቻይና መንግሥት ለኢትዮጵያ ፖሊስ በተለያዩ የሙያ መስኮች የትምህርት እና ስልጠና እድል እየሰጠ እንደሚገኝ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገልፀው ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።


 

ኮሚሽነር ጀነራሉ አያይዘዉም የቻይና ባለሀብቶች በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በተሰማሩባቸዉ የልማት ስራዎች ላይ የተለያዩ ፀረ ሰላም ኃይሎች ጉዳት እንዳያደርሱ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስፈላጊዉን ጥበቃ እያደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

አዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ ህብረት እና የተለያዩ አለም ሀገራት ዲፕሎማቶች መቀመጫ እንደመሆኗ ፀጥታዋ አስተማማኝ አንዲሆን የፀጥታ አካላት ከነዋሪው ሕዝብ ጋር ተቀናጅተው በመስራት ላይ ናቸው ሲሉም ኮሚሽነር ጀነራሉ አክለዋል።


 

የቻይና ሕዝብ ደህንነት ምክትል ሚኒስትር ዡ ዳቶንግ በበኩላቸው የቻይና የልማት ፕሮጀክቶች ደኅንነት እንዲጠበቅ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጋር ተቀራርበው እንደሚሰሩ በዉይይቱ ላይ አንስተዋል።

ምክትል ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እየተከናወኑ ያሉ የለውጥ ተግባራትን ጎብኝተው ተቋሙን ለማዘመን እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ማድነቃቸውን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም