ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ለማስፋትና ለማጠናከር እየሰራች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ለማስፋትና ለማጠናከር እየሰራች ነው
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 13/2016 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ ወዳጅ የማብዛት ዲፕሎማሲን መሰረት በማድረግ ከተለያዩ አገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ለማስፋትና ለማጠናከር እየሰራች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
16ኛው የቻይና-አፍሪካ የትብብር ፎረም (ፎካክ) የከፍተኛ ኃላፊዎች ስብሰባ ትናንት በቻይና ቤጂንግ ተካሄዷል።
በፎረሙ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2021 በሴኔጋል ርዕሰ መዲና ዳካር በተካሄደው ስምንተኛው የፎካክ የሚኒስትሮች ጉባኤ ቻይና ለአፍሪካ ይፋ ያደረገቻቸው ዘጠኝ ፕሮግራሞች የአፈጻጸም ሂደት ምክክር ተደርጎበታል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠጠር በ2024 የሚካሄደው የፎካክ ፎረም ዝግጅትን አስመልክቶም ምክክር ተደርጓል።
ኢትዮጵያ ፎካክ ከተመሰረተ ጊዜ አንስቶ በማዕቀፉ ጠንካራ ተሳትፎ እያደረገች እንደምትገኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ፣ ኤዥያና ፓሲፊክ አገራት ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ገበየሁ ጋንጋ (ዶ/ር) ለኢዜአ ገልጸዋል።
ጤና፣ ድህነት ቅነሳ፣ ሰላምና ጸጥታ፣ ባህልና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ጨምሮ በፎረሙ አማካኝነት እየተተገበሩ ካሉት ዘጠኝ የትብብር ፕሮግራሞች ተጠቃሚ መሆኗን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በመርኃ ግብሮቹ ያላትን ልምድ ለሌሎች የአፍሪካ አገራት እያካፈለች እንደምትገኝም ነው አምባሳደሩ የገለጹት።
ኢትዮጵያ ወዳጅ የማብዛት ዲፕሎማሲን መሰረት በማድረግ ከተለያዩ አገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ለማስፋትና ለማጠናከር እየሰራች መሆኑን ጠቁመዋል።
የዲፕሎማሲ አካሄዱ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የቻይና ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ፎካክን የሚከታተለው የቻይና ኮሚቴ ሊቀ-መንበር ዴንግ ሊ በበኩላቸው የቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ የቻይናና አፍሪካ ግንኙነትን ከማጠናከር አኳያ ስኬታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ትብብሩ ወዳጅነትና ትብብርን ማጠናከር እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነትና መግባባት ላይ የተመሰረተ መሆኑን አመልክተዋል።
ቻይና በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሺዬቲቭና በሌሎች የዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ማዕቀፏቿ አማካኝነት ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ትብብር ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር በጋራ መሥራቷን ትቀጥላለች ብለዋል።
በፎረሙ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2022 የቻይናና አፍሪካ የንግድ ልውውጥ 282 ቢሊየን ዶላር መድረሱ ተገልጿል።
የቻይና አፍሪካ የትብበር ፎረም (ፎካክ) የቻይናና አፍሪካን ግንኙነት ለማጠናከር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2000 የተመሰረተ የባለ ብዙ ወገን የትብብር ማዕቀፍ ነው።
ትላንት በተካሄደው ፎረም በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበውን ጨምሮ የቻይናና አፍሪካ አገራት መንግሥት ተወካዮች ተሳትፈዋል።