ቀጥታ፡

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከመቼውም ጊዜ በላይ በአስተማማኝ ብቃትና ዝግጁነት ላይ ይገኛል

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 13/2016 (ኢዜአ)፦የሀገርን ክብርና ሉዓላዊነት በማስጠበቅ ረገድ መከላከያ ሰራዊት ከመቼውም ጊዜ በላይ በላቀ ብቃትና ዝግጁነት ላይ ይገኛል።

የ116ኛ የሰራዊት ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ይገኛል። 


 

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት ጄነራል ጌታቸው ጉዲና፤ ለኢትዮጵያ ታሪክ መጠበቅና ሉዓላዊነት መከበር የሰራዊቱ ሚና እና ታላቅ ተጋድሎ የጎላ ስፍራ የሚሰጠው ነው ብለዋል።   

የኢትዮጵያን ሀገረ-መንግስት በማጽናት ሂደት የሠራዊቱ አስተዋጽኦና የከፈለው መስዋእትነት በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም ሲሉም ተናግረዋል።

የሀገርን ክብርና ሉዓላዊነት በማስጠበቅ ረገድ መከላከያ ሰራዊት ከመቼውም ጊዜ በላይ በአስተማማኝ ብቃትና ዝግጁነት ላይ ይገኛል ብለዋል።

የፓናል ውይይቱም የሰራዊቱን ሀገር የማጽናት ብቃት እና የፈፀማቸው ገድሎቹ የሚዘከሩበት መሆኑን ገልጸዋል።


 

በመድረኩ የመከላከያ ሰራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖች፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ተወካዮች፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት አመራሮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። 

116ኛው የሠራዊት ቀን "በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የፀና የድል ሠራዊት" በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ሲሆን ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከበር ይሆናል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም