ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ በላቀ ብቃትና ጀግንነት የሀገራቸውን ክብር ያስጠበቁ በርካታ የሀገር ባለውለታዎችን ያፈራ ተቋም ነው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 13/2016 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ በላቀ ብቃትና ጀግንነት የሀገራቸውን የአየር ክልል ያስጠበቁ በርካታ የሀገር ባለውለታዎችን ያበረከተና አሁንም እያፈራ ያለ ተቋም ነው።


 

የኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ የመሰረታዊ ውትድርና ማሰልጠኛ፣ የቴክኒክ፣ የበረራና የአመራር ትምህርት ቤቶችን ይዟል።

የአየር ሃይል አካዳሚ ከ70 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረና ሀገር የምትኮራባቸውን በርካታ ጀግኖች ያፈራ ስመ ጥር ትምህርት ቤት ነው፡፡


 

በቀጣይም አየር ኃይሉ በአፍሪካ ቀዳሚ ለመሆን የያዘውን ራዕይ ለማሳካት የትምህርት ቤቱ ቀጣይነት ያለው ብቁ የሰው ሃብት የማፍራት ስራ ወሳኝ መሆኑ ይታመናል።

የአየር ሃይል በረራ ትምህርት ቤት አዛዥ ኮሎኔል ጃምቦ አዛገ፤ ትምህርት ቤቱ የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት ያስከበሩና እያስጠበቁ ያሉ በርካታ ጀግና አብራሪዎችን ያፈራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በሱማሌ ጦርነት በነበረው ሀገርን ከጠላት የመጠበቅ ትግል በአየር ላይ ውጊያ ታላላቅ ጀብድ የፈፀሙ ጀግኖችን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ከጀማሪ እስከ ከፍተኛ ሙያ ባለቤት የሆኑ ጀግና አብራሪዎችን አሁንም ትምህርት ቤቱ እያፈራ መሆኑን በመጥቀስ፡፡

የስልጠና ሂደቱም በቴክኖሎጂ የተደገፈ እና በዲጅታል ሲስተም የታገዘ መሆኑን ጠቅሰው አውሮፕላኖቹም የተሟላ ቴክኖሎጂ የተገጠመላቸው መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡


 

ከበረራ ትምህርት ቤቱ ተማሪዎች መካከል ሲኒር ካዴት ዋንጋሪ አበራ እና ምክትል መቶ አለቃ ገብረ መድህን ተመስገን፤ ለኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት ማንኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

የአየር ሃይል አካዳሚ ዋና አዛዥ ኮሌኔል ገዛኸኝ ነጋሽ፤ አየር ሃይሉ በ2030 ከአፍሪካ ቀዳሚ አየር ሃይል የመሆን ራዕይ ሰንቆ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።


 

ለዚህም የአየር ሀይል አካዳሚ ትልቁን ድርሻ መያዙን ጠቅሰው አመራሮችን፣ ቴክኒሻኖችንና አብራሪዎችን የተሟላ ብቃት እንዲኖራቸው በማድረግ ለሀገር የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል፤ የኢትዮጵያ አየር ክልል አስተማማኝ ዘብ በመሆን ከጥንት እስከ ዛሬ የሀገር ኩራት ሆኖ ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም