ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሪስክ ካፓሲቲ ካምፓኒ (ARC)ን መቀላቀል የሚያስችላትን ስምምነት ተፈራረመች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሪስክ ካፓሲቲ ካምፓኒ (ARC)ን መቀላቀል የሚያስችላትን ስምምነት ተፈራረመች
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 13/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሪስክ ካፓሲቲ ካምፓኒ (ARC) የአፍሪካ ህብረት ኤጀንሲን መቀላቀል የሚያስችላትን ስምምነት ተፈራርማለች።
በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሬታ ሰዋሰው፣ በሚስተር ሞሀመድ ሳሌም የተመራ የአፍሪካ ህብረት ልዑክ፣ እና የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ተወካዮች ተገኝተዋል።
ኢትዮጵያን በመወከል የስምምነት ፊርማውን የፈረሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ሲሆኑ የስምምነቱን ጠቀሜታ በተመለከተም ንግግር አድርገዋል።
በንግግራቸውም ስምምነቱ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሪስክ ካፓሲቲ ካምፓኒ ጋር በጋራ በመስራቷ የተሻለ ዝግጁነት፣ ዕቅድ ዝግጅት፣ የከፋ የአየር ክስተትና የተፈጥሮ አደጋዎች ላይ የተሻለ አቅም መገንባት ያስችላታል ብለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያ እያስከተለ ያለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ኢትዮጵያ በዘርፉ ከሚሰሩ እንደ የአፍሪካ ሪስክ ካፓሲቲ ኢንሹራንስ ካምፓኒ ካሉ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ጋር በትብብር ትሰራለች ብለዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ አክለውም መንግስት ብሄራዊ የአደጋ ምላሽ አሰጣጥ አቅምን ለማሳደግ ከአፍሪካ ሪስክ ካፓሲቲ ኢንሹራንስ ጋር ለመስራት ቁርጠኛ ነውም ብለዋል።
የአፍሪካ ህብረትን ልዑክ በመምራት በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት ሚስተር ሞሀመድ ሳሌም ቡኩሃሪ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት የአፍሪካ ሪስክ ካፓሲቲ ኢንሹራንስን ለመቀላቀል መፈራረሙ በአየር ንብረት ለውጥ የሚመጣውን አደጋ ለመቀነስ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።