ኢትዮጵያ በመርሆዎች መግለጫ ስምምነት መሰረት በሚደረግ ውይይት አዎንታዊ ውጤት ላይ መድረስ እንደሚቻል ታምናለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በመርሆዎች መግለጫ ስምምነት መሰረት በሚደረግ ውይይት አዎንታዊ ውጤት ላይ መድረስ እንደሚቻል ታምናለች
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በመርሆዎች መግለጫ ስምምነት መሰረት በሚደረግ ውይይት አዎንታዊ ውጤት ላይ መድረስ እንደሚቻል ኢትዮጵያ ታምናለች ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሦስተኛው ዙር የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አሞላል እና ዓመታዊ የውሃ አለቃቀቅ ደንብ እና መመሪያን በሚመለከት የሚካሄደው የሦስትዮሽ ውይይት ዛሬ ጥቅምት 12 ቀን 2016 ዓ.ም. በካይሮ፣ ግብጽ ተጀምሯል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሦስትዮሽ ውይይቱን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።
በመርሆዎች መግለጫ ስምምነት መሰረት በሚደረግ ውይይት አዎንታዊ ውጤት ላይ መድረስ እንደሚቻል ኢትዮጵያ ታምናለች ሲል የሚኒስቴሩ መግለጫ ያመለክታል።
በዚህም መሰረት በዚህ በድርድሩ ሂደት ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ውጤት እንዲመጣ ለማስቻል ሀገራችን በቅን ልቦና ትካፈላለች።
ይህ ውይይት ሶስቱ ሀገራት ጠንካራ አጋርነት ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት አካል ሲሆን፣ በዚህ ሂደት ሀገራቱ የዓባይን ወንዝ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም የማረጋገጥ የጋራ ኃላፊነት አለባቸው።
እነዚህ ውይይቶች ሦስቱ አገራት የሁሉንም ፍላጎት የሚያስጠብቁ የመግባቢያ ሃሳቦችን በማፍለቅ በትብብር እንዲሰሩ ያስችላቸዋል።
አገራቱ የሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት ጥቅምና ስጋቶች ተረድተው በፍትሐዊ እና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት መርህ ላይ በመመስረት ከተደራደሩ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ላይ እንደሚደርሱ ታምናለች ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው አስታውቋል።