25ኛው የምሥራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ጥቅምት 14 በቡጁንቡራ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
25ኛው የምሥራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ጥቅምት 14 በቡጁንቡራ ይካሄዳል
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 12/2016 (ኢዜአ) ፦ 25ኛው የምሥራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ከጥቅምት 14 ቀን 2016 ጀምሮ በቡሩንዲ ዋና ከተማ ቡጁንቡራ ይካሄዳል።
ጠቅላላ ጉባኤው "leveraging on the regional policing capabilities in promoting law enforcement cooperation in the fight against terrorism and transnational organized crime" በሚል መሪ ሀሳብ በቡሩንዲ አስተናጋጅነት በቡጁምቡራ ከተማ እንደሚካሄድ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በጠቅላላ ጉባኤው ኢትዮጵያን ጨምሮ ሁሉም የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት አባል ሀገራት ፖሊስ አዛዦች እና ዓለም አቀፍ የፀጥታ እና ደህንነት ተቋማት ተወካዮች እንደሚሳተፉ ተመላክቷል።
የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት የቋሚ አስተባባሪ ኮሚቴ እና በሥሩ ያሉ የህግ፣ የፀረ-ሽብር፣ የትምህርትና ስልጠና፣ የሥርአተ ጾታ፣ የሳይበር ደኅንነት የቴክኒካል ንዑስ ኮሚቴዎች በዛሬው ዕለት የጋራ ስብሰባ እና የተናጠል ውይይቶችን እያደረጉ እንደሚገኙም ተጠቅሷል።
የቴክኒካል ንዑስ ኮሚቴዎች የሚደርሱበትን ውጤትም በፖሊስ መሪዎች ጠቅላላ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ አቅርበው ልዩ ልዩ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉም ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ አዛዥና የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት ቋሚ አስተባባሪ ኮሚቴ ሊቀ-መንበር ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግሥቴ በጋራ ስብሰባው ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ተቀናጅቶ ለመከላከል አባል ሀገራት ተሞክሯቸውን በማካፈል እና ለሚስተዋሉ ችግሮች የጋራ መፍትሄ በማስቀመጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።