ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙሃን ብሔራዊ ጥቅምን በተመለከተ በዜጎች መካከል የጋራ አቋም እንዲኖር በኃላፊነት ሊሰሩ ይገባል

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 12/2016 (ኢዜአ) ፦ መገናኛ ብዙሃን ብሔራዊ ጥቅምን በተመለከተ በዜጎች መካከል የጋራ አቋም እንዲኖር በኃላፊነት ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ።

አገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስከበር ከሚጠቀሙባቸው ዘርፎች መካከል መገናኛ ብዙሃን አንዱ መሆኑ እሙን ነው።

በተለይ መገናኛ ብዙሃን ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ዜጎች የጋራ አቋም ይዘው እንዲሰሩ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ሚና አላቸው።

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህር ተስፋዬ አለማየሁ፤ ብሔራዊ ጥቅምን የሚመለከቱ ጉዳዮች የአንድ ሰሞን ዘመቻ ሳይሆኑ በቀጣይነት ሊሰራባቸው ይገባል ይላሉ።

ለዚህ ደግሞ መገናኛ ብዙሃን የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ትክክለኛ መረጃ ለህብረተሰቡ ማድረስ እንዳለባቸው ነው ያብራሩት።

ለአብነትም የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄን በተመለከተ ዜጎች የጋራ አቋም ይዘው እንዲሰሩ በማድረግ በኩል ከመገናኛ ብዙሃን ቀጣይነት ያለው ስራ ይጠበቃል ብለዋል።

ጥያቄው አሁን ኢትዮጵያ የደረሰችበትን የኢኮኖሚ ዕድገትና የህዝቡን የልማት ፍላጎት መሰረት ያደረገ በመሆኑ በተከታታይ ሊሰራበትና የጋራ ግንዛቤ ሊያዝበት እንደሚገባም አንስተዋል።

በተመሳሳይ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህር ኢብራሂም አብደላ፤ መገናኛ ብዙሃን ብሔራዊ ጥቅምን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ በትኩረትና በጥልቀት በመስራት የበኩላቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄውን ለምን ማንሳት እንደፈለገች እውነተኛና ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ሀሳቡ በተሳሳተ መንገድ እንዳይተረጎም ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

መገናኛ ብዙሃን ዜጎች በአንድ ጉዳይ ላይ ግልጽ የሆነ መረዳት እንዲኖራቸው በመስራት በኩል ክፍተት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ አጀንዳ ቀርጸው ብዥታን የሚያጠሩ መረጃዎችን መስጠት አለባቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም