የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለኢትዮጵያ አየር ክልል አስተማማኝ ዘብ ከመሆን ባሻገር በልማት ስራዎች ላይ አብነት የሚሆን ተግባር እያከናወነ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለኢትዮጵያ አየር ክልል አስተማማኝ ዘብ ከመሆን ባሻገር በልማት ስራዎች ላይ አብነት የሚሆን ተግባር እያከናወነ ይገኛል
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 12/2016 (ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለኢትዮጵያ አየር ክልል አስተማማኝ ዘብ ከመሆን ባሻገር በልማት ስራዎች ላይ አብነት የሚሆን ተግባር እያከናወነ መሆኑ ተገለጸ ፡፡
የኢትዮጵያ አየር ኃይል በዘመናዊ ትጥቅና በብቁ የሰው ኃይል በመደራጀት ለኢትዮጵያ አየር ክልል አስተማማኝ ዘብ ሆኖ ተገንብቷል፡፡
አየር ኃይሉ በተለይ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ ከፍተኛ ስራ እያከናወነም ይገኛል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን በቅጥር ግቢው ውስጥ በ74 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ ሰብሎችን አትክልትና ፍራፍሬዎች በማልማት ላይ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ አየር ኃይል የውበትና ልማት መምሪያ ሃላፊ ሌተናል ኮሎኔል ምስጋኑ ለገሰ እንደሚሉት፤ተቋሙ የምግብ ፍጆታውን በራሱ ምርት ለመሸፍን በማለም የልማት ሰራዎችን በስፋት በማከናወን ላይ ነው፡፡
በዚህም በተቋሙ ቅጥር ግቢ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ሽምብራ፣ ቦሎቄ እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬዎችን የማልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አየር ኃይሉ የሚያለማቸውን ምርቶች በግቢው ውስጥ ለሚገኙ ወታደራዊ እና ሲቪል ሰራተኞች በአነስተኛ ዋጋ በማቅረብ ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ለበርካታ የአከባቢው ማህበረሰብ ክፍሎችም ስራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረው በቀጣይ የልማት ስራዎችን ለማስፋት እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡
የቀድሞ የአየር ሃይል አባል እና በአሁን ጊዜ የልማት ሰራተኛ የሆኑት ሻለቃ ባሻህ መሐመድ፤ ከዚህ ቀደም በአየር ሃይል ግቢ ውስጥ የሚገኘው ሰፊ መሬት ጦሙን የሚድር እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት ግን ለሌሎች ተቋማት አብነት የሚሆን የልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
አየር ኃይሉ በሚያከናወነው የልማት ስራ ላይ የስራ እድል የተፈጠረላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ወጣት ፍቃዱ አበበ፤ ከዚህ ቀደም ስራ አጥ እንደነበር ጠቅሶ፤ አሁን ላይ በሚያገኘው ገቢ ቤተሰቡን እንደሚደግፍ ተናግሯል፡፡
ወርቅነሽ ምትኩ በበኩሏ ከደመወዝ ባሻገር ምርቶችን በአነስተኛ ዋጋ በመግዛት ተጠቃሚ መሆኗን ተናግራለች፡፡
አየር ኃይሉ በቀጣይ የልማት ስራውን በማስፋት ከሰራተኛው ባሻገር የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራም ነው የገለጸው፡፡