የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በድል በመሻገር የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት እናስከብራለን - ኢዜአ አማርኛ
የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በድል በመሻገር የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት እናስከብራለን
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 11/2016 (ኢዜአ)፦ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በድል በመሻገር የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት ለማስከበር ከየትኛውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆናቸውን የኢትዮጵያ አየር ኃይል አመራርና አባላት ገለጹ።
116ኛ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የምስረታ ቀን በመጪው ሀሙስ የሰራዊቱን ተጋድሎና ጀግንነት በሚዘክሩ በተለያዩ መርሐ ግብሮች ይከበራል።
ኢዜአ ቀኑን በማስመልከት ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ አየር ኃይል አመራርና አባላት በሰራዊት ቀን ለህዝባችንና ለሀገራችን ደህንነት ህይወታችንን ለመስጠት የገባነውን ቃል ዳግም እናረጋግጣለን ብለዋል።
የአየር ኃይል ጥበቃ ክፍለ ጦር አዛዥ ኮሎኔል ወንዱ ወልዴ፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ከመቸውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የእድገት ግስጋሴ ያልተመቻቸው የውስጥና የውጭ ኃይሎችን የጥፋት ሙከራ በመመከት ክብርና ሉአላዊነቷን ለመጠበቅ ተዘጋጅተናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል በሁሉም ዘርፍ ኢትዮጵያን በሚመጥን መልኩ በላቀ ሁኔታ እየተደራጀ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ አየር ኃይል የሱ-27 ዘመናዊ ተዋጊ ጄት ቴክኒሺያን ሊ ኤግ ኤርክራፍትማን አብዲ ደራርሶ፤ በየትኛውም ሁኔታ ኢላማውን የሚመታ የተሟላና ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አቅም እየተገነባ መሆኑን ገልጿል።
የአየር ኃይሉ አስፈላጊውን ግዳጅ በብቃት እንዲወጣም እርሱና ባልደረቦቹ አስተማማኝ የፍተሻና ጥገና ስራ በማካሄድ ለሀገራቸውን ጉልህ ሚና እየተወጡ እንደሚገኙ ገልጿል።
የሀገርን ክብርና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በተሰማሩበት የውትድርና መስክ 24 ሰዓት በማገልገል ላይ መሆናቸውን ገልጿል።
አየር ኃይልና ሌሎች የሀገር መከላከያ ሰራዊት ክፍሎች የኢትዮጵያ የመጨረሻ ምሽግ ናቸው ያለው ሊ ኤግ ኤርክራፍትማን አብዲ፤ ሀገርን፣ ህዝብንና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በአስተማማኝ ሁኔታ እንጠብቃለን ብሏል።
ጠንካራ ሰራዊት፣ የተደራጀና ዘመናዊ ትጥቅ፣ እንዲሁም አይበገሬ ኢትዮጵያዊ ስነልቦና ያለን በመሆኑ ፈተናዎችን በድል እየተሻገርን የኢትዮጵያን ዳር ድንበሯን እናስከብራለን ነው ያለው።
ሌላኛዋ የሱ 27 ጄት የጥገና ክፍል ባልደረባ ሃምሳ አለቃ ጋዲሴ ገመቹ ወደ ሰራዊቱ የገባነው፤ እናት ሀገራችን ተከብራ እንድትኖር የትኛውንም ዋጋ ለመክፈል ነው በዚህም ደስተኞች ነን ትላለች።
በቀጣይም ሠራዊቱ የሀገርን ሰላም የማስጠበቅ ግዳጅና ተልዕኮን በብቃት እንዲፈጽም በተሰማራችበት ሙያ ሌት ተቀን በመትጋት የበኩሏን እንደምትወጣም አረጋግጣለች።