ቀጥታ፡

በዳሰነች ወረዳ በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች ዘላቂ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያግዙ ሁለት ፕሮጀክቶች ወደ ስራ ሊገቡ ነው

ጂንካ፤ጥቅምት 11/2016 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት ዘላቂ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ሁለት ፕሮጀክቶች ወደ ስራ ሊገቡ እንደሆነ ተገለጸ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ለድርቅና ለጎርፍ ተጋላጭ ከሆኑ ወረዳዎች አንዱ የሆነው የዳሰነች ወረዳ ባለፉት አመታት ለድርቅ ተጋልጦ ነበር።

እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ መንግስትና አጋር ድርጅቶች የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ ጊዜያዊ የሰብአዊ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር ዘላቂ የልማት ስራዎችን በአከባቢው እያከናወኑ ይገኛሉ።

በዛሬው ዕለትም 'አግሪ ሰርቪስ ኢትዮጵያ' የተሰኘ ሀገር በቀል ድርጅት ዘላቂ የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ጥረት ያግዛሉ የተባሉ ሁለት ፕሮጀክቶች የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።

አንደኛው ፕሮጀክት ተጎጂዎችን መልሶ የማቋቋም ስራዎች የሚሰራበት ሲሆን 549 ፍየሎችን ለ183 እማወራና አባወራዎች ለማከፋፈል ታቅዷል።

በተጨማሪም 100 ለሚሆኑ አባወራዎች ደግሞ 500 ዕንቁላል ጣይ ዶሮዎች የሚሰጡ ሲሆን ለእያንዳንዱ 5 ዶሮ ይከፋፈላል።

ሁለተኛው ፕሮጀክት ደግሞ የጓሮ አትክልት፣ ፍራፍሬ እና የሰብል ዘሮች አርብቶ አደሩ በመስኖ እንዲያለማ በመደገፍ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንዲችል ማገዝ ነው ተብሏል።

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳደር ልዩ አማካሪ አቶ መሰለ መስፍን፣ በዞኑ ቆላማ አካባቢዎች በተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ በርካታ አርብቶ አደሮች ለማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መጋለጣቸውን ገልፀዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖውን ለመቋቋም በመንግስት የተነደፉ ዘላቂ የልማት ግቦች ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች እየተተገበሩ መሆናቸውን አንስተው በዚህም በአካባቢው ላይ ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑም አመላክተዋል።

ዛሬ የተጀመሩ ሁለት ፕሮጀክቶችም በአካባቢው ድርቅን ለመቋቋም እና ዘላቂ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚሰሩ የልማት ስራዎችን ውጤታማ በማድረግ ረገድ ሚና እንደሚኖራቸው አንስተዋል።

ፕሮጀክቶቹ በአርብቶ አደሩ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ በመሆናቸው ለውጤታማነቱ የዞኑ አስተዳደር የማያቋርጥ ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

የ'አግሪ ሰርቪስ ኢትዮጵያ' ዋና ማዕከል የፕሮግራም ኃላፊ አቶ ሚካኤል ጆን በዛሬው ዕለት የተጀመሩና በዳሰነች ወረዳ በ10 ቀበሌዎች የሚተገበሩ ፕሮጅክቶች ዘላቂ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያግዙ ናቸው ብለዋል።

ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት የሚተገበሩት ፕሮጀክቶቹ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ላይ ያተኮሩት ሲሆን ከ4 ሺህ 500 በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደርጋሉ ነው ያሉት።

አካባቢው ለረጅም አመታት የዘለቀው ድርቅና ተያያዥ የተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ በተለይ ሴቶችና ህፃናት ይበልጥ ተጋላጭ መሆናቸውን ያነሱት የደቡብ ኦሞ ዞን ሴቶችና ህፃናት መምሪያ ተወካይ ወይዘሮ አሚዳ ሰኢድ ናቸው።

እነዚህ ፕሮጀክቶቹ ለአየር ንብረት ለውጡ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ በተለይ  ሴቶችን እና ህፃናትን ከግምት ውስጥ ያስገቡ መሆናቸው ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል።

የዳሰነች ወረዳ የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሳምነው ደምሴ በበኩላቸው በወረዳው ለረጅም አመታት ተከስቶ በነበረው ድርቅ በሰው፣በእንስሳት እና በሰብሎች ላይ ጉዳት ማድረሱን አንሰተዋል።

ድርቁን ተከትሎ በቅርቡ በተከሰተው የኦሞ ወንዝ ያልተጠበቀ ሙላት የጎርፍ አደጋ መከሰቱንና በርካታ አርብቶ አደሮች ለጉዳት መጋለጣቸውን ገልፀዋል።

በአሁኑ ሰአት በመንግስትና በአጋር ድርጅቶች ለተጎጂዎች የምግብ ድጋፍ እየቀረበ ቢሆንም ከጉዳቱ ስፋት አኳያ ድጋፉ በቂ አለመሆኑን ገልፀዋል።

አርብቶ አደሩን በዘላቂነት ለማቋቋም ከሚሰሩ የልማት ስራዎች ጎን ለጎን የሰበአዊ ድጋፎችም ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ኃላፊው ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም