ሠራዊቱ በየትኛውም የግዳጅ ቀጣና የሚሰጠውን ተልዕኮ በብቃትና በአሸናፊነት ለመወጣት በሚችልበት ቁመና ላይ ነው -- ሌተናል ጄኔራል ዘውዱ - ኢዜአ አማርኛ
ሠራዊቱ በየትኛውም የግዳጅ ቀጣና የሚሰጠውን ተልዕኮ በብቃትና በአሸናፊነት ለመወጣት በሚችልበት ቁመና ላይ ነው -- ሌተናል ጄኔራል ዘውዱ
ጋምቤላ፤ ጥቅምት 11/2016(ኢዜአ)፦ሠራዊቱ በየትኛውም የግዳጅ ቀጣና የሚሰጠውን ተልዕኮ በብቃትና በአሸናፊነት ለመወጣት በሚችልበት ቁመና ላይ ነው ሲሉ የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ዘውዱ በላይ ተናገሩ።
116ኛው የኢትዮጵያ ሠራዊት ቀን ''በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የሚፀና የድል ሠራዊት!'' በሚል መሪ ሀሳብ በጋምቤላ ክልል በፓናል ውይይት ተከብሯል።
በኢፌዴሪ የአገር መከላከያ ሰራዊት የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ዘውዱ በላይ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ሠራዊት ባለፈው አንድ ክፍለ ዘመን ለአገሩ ሉዓላዊነት መስዋዕትነትን እየከፈለ መጥቷል።
በኢትዮጵያ የህግ የበላይነት እንዲሰፍንና ህዝቦቿ ሰላም እንዲሆኑ በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ የተቻለውን ሁሉ አስተዋጽኦ ሲያበረክት የኖረ ሠራዊት መሆኑንም ተናግረዋል።
ሠራዊቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ ባለፈ በሌሎች አገሮች ሰላም ለማስከበር በተካፈለባቸው ግዳጆች ሁሉ አኩሪ ገድል ሲፈፅም መኖሩን አብራርተዋል።
አሁንም ሠራዊቱ በየትኛውም የግዳጅ ቀጣና የሚሰጠውን ተልዕኮ በብቃትና በአሸናፊነት ለመወጣት በሚችልበት ቁመና ላይ ያለ መሆኑን ተናግረዋል።
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡመድ ኡጁሉ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ የአገር መከላከያ ሠራዊት ከውጪም ሆነ ከውስጥ የሚገጥማትን ፈተና በድል በመሻገር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትን አፅንቶ ቆይቷል።
ሠራዊቱ ዓለም የደረሰበትን ከፍተኛ ቴክኖሎጂ በመላበስ በሁሉም አውደ ውጊያ ብቁና የአሸናፊነት ስነ-ልቦናን የገነባ መሆኑን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ሠራዊት ቀን በዚህ መልኩ መከበሩ በአገርና በህዝብ ላይ የሚያጋጥሙ አደጋዎችን በላቀ ጀግንነት ለመመከት የሠራዊቱን ሞራል የሚገነባ እንደሆነም ተናግረዋል።
የሠራዊት ቀን ሲከበር ሠራዊቱ ለአገር ሉዓላዊነትና ለህዝብ ሰላም ለከፈለውና እየከፈለ ላለው መስዋዕትነት ያለንን አክብሮት የምንገልጽበት ጭምር ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የአገርን ዳር ድንበርና ሰላም ለማስጠበቅ ለሚያደርገው ተጋድሎ የክልሉ መንግስት ከሠራዊቱ ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።
የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ባንቻየሁ ድንገታ በበኩላቸው፤ ሠራዊቱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የአገር ሉዓላዊነትን የሚያስከብርና እያስከበረ ያለ መሆኑን አብራርተዋል።
በተለይም የኢትዮጵያ ሠራዊት የአገርን ዳር ድንበር ከማስከበር ጎን ለጎን በተለያዩ የልማት ስራዎች ላይም በመሳተፍ የህዝብ አለኝታነቱን በተግባር ማሳየቱንም ተናግረዋል።
በፓናል ውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ሠራዊት ታሪካዊ ዳራ፣ የሠራዊቱ እድገትና ለውጥ እንዲሁም በሠራዊቱ ተጋድሎ የተገኙ ድሎች ላይ የመነሻ ፅሁፍ ቀርቦ ውይይቶች ተካሂደዋል።