ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ላይ ከውስጥና ከውጭ የሚቃጣ ጥቃትን በሩቁ የሚያስቀር ሠራዊት በሁሉም መስክ እየተገነባ ነው-ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 11/2016 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ላይ ከውስጥና ከውጭ የሚቃጣ ጥቃትን በሩቁ የሚያስቀር ሠራዊት እየተገነባ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ ገለፁ። 

116 ኛው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ቀን "በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የሚፀና የድል ሠራዊት" በሚል መሪ ሀሳብ በኢትዮጵያ አየር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ተከብሯል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አየር  ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ፣ የአየር ኃይሉ ከፍተኛ አመራሮችና አባላት ተገኝተዋል።


 

ሌተናል ጀነራል ይልማ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ሠራዊቱ በውስብስብና ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ሁሉ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሟንና ሉዓላዊነቷን በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስከበር መሆኑን ተናግረዋል።

የሠራዊት ቀን ሲከበር ህዝቡ ለሠራዊቱ እውቅና  የሚሰጥበትና የሠራዊት አባላት ደግሞ ለሀገርና ለህዝብ ደህንነት ህይወታቸውን ለመስጠት ዳግም ቃል የሚገቡበት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የገናና ታሪክ ባለቤት መሆኗን ጠቅሰው ከነገሥታቱ ጊዜ ጀምሮ ሠራዊቱ ከፍተኛ ተጋድሎዎችን በመፈጸም ሀገር ማጽናቱን አስታውሰዋል።

በሁሉም አቅሞች የውጊያ ዝግጁነትን በማረጋገጥ ኢትዮጵያ እንዳትደፈር የሚያስችል ጠንካራ ሠራዊት አየር ኃይልን ጨምሮ በሁሉም አውዶች እየተደራጀ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

የኢትዮጵያ አየር ኃይልን በዘመናዊ ተዋጊ አውሮፕላኖች፣ በቴክኖሎጂ፣ ብቃት ባለው  የሰው ኃይልና በመሠረተ ልማት የማደራጀት  ተግባራት  ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅሰዋል። 

በአየር ኃይል ጠቅላይ  መምሪያ የተገነቡ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች በዛሬው ዕለት ተመርቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም