ቀጥታ፡

የሰራዊቱን ግዳጅ የመፈጸም ተልዕኮውን የሚያጎለብቱ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 10/2016(ኢዜአ)፡- የሰራዊቱን ግዳጅ የመፈጸም ተልዕኮውን የሚያጎለብቱ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ። 

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በመከላከያ መሃንዲስ ዋና መምሪያ የተገነቡትን የመከላከያ መረጃ ማዕከል መሰረተ ልማትና የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ የአየር ወለድ ማሰልጠኛ ማዕከልን መርቀው ከፍተዋል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የምህንድስና መምሪያ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሰፋፊ ሥራዎችን እያከናወነ ነው።

የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ የአየር ወለድ ማሰልጠኛ ማዕከል ከዚህ ቀደም መሰረተ ልማት የተሟላለት እንዳልነበር አስታውሰው አሁን ላይ ደረጃውን ጠብቆ መገንባቱን ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ የመከላከያ መረጃ ማዕከል መሰረተ ልማት በተገቢው መልኩ መገንባቱንም ጠቅሰዋል።  

ለሁለቱም ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ አስተዋጽዖ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበው በቀጣይ ጊዜያትም የሰራዊቱን ግዳጅ የመፈጸም ተልዕኮውን የሚያጠናክሩ ሥራዎች ይሰራሉ ብለዋል። 


 

የመከላከያ መረጃ ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄኔራል ጌታቸው ጉዲና የሰራዊቱ የለውጥ አመራር የጀመራቸውን ሥራዎች እያጠናቀቀ ውጤቱንም እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ሰራዊቱን እየገነባ የአገር ዋልታ የሆነ ተቋም መሆኑን ገልጸው ለምርቃት የበቃው የመከላከያ መረጃ ማዕከል መሰረተ ልማት ትልቅ አቅም መሆኑን ጠቁመዋል። 


 

የመከላከያ መሃንዲስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ደስታ አብቼ መምሪያው የሰራዊቱ የግዳጅ አፈጻጸሞ እንዲያድግ ውጤታማ ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።

በ2015 በጀት ዓመት 60 ፕሮጀክቶች ለተጠቃሚው ክፍሎች መተላለፋቸውን ገልጸው በ2016 በጀት ዓመትም ትልልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች እንደሚገነቡ ጠቁመዋል።

ለምርቃት የበቁት ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ በራስ አቅም መገንባታቸውን ገልጸው ፕሮጀክቶቹ ዘመናዊና ለበለጠ ሥራ የሚያነሳሱ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

 

የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ የአየር ወለድ ማሰልጠኛ ማዕከል በዚህ መልክ ለአገልግሎት ያበቁ አካላትን አመስግነዋል።

ተከታታይ ሥልጠናዎች ለሰራዊቱ አባላት በመስጠት የአገርና የሕዝብን ደኅንነት የሚጠብቅ ሠራዊት ለመገንባት ትኩረት እንደሚደረግ አረጋገጠዋል።  

በመርኃ ግብሩ ማጠናቀቂያ የመከላከያ መረጃ ዋና መምሪያና የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ የቁልፍ ርክክብ የተካሄደ ሲሆን ለፕሮጀክቶቹ መጠናቀቅ አስተዋጽዖ ላበረከቱ አካላት እውቅና ተሰጥቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም