ቀጥታ፡

 የአዳማ ከተማ አስተዳደር  የነዋሪዎችን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በአግባቡ ለመመለስ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

አዳማ ፤ ጥቅምት 10/2016(ኢዜአ)፡-  የአዳማ ከተማ አስተዳደር የነዋሪዎችን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በአግባቡ በመመለስ የህዝብ እርካታን ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።  

በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ሙሁራን በምስራቅ ሸዋ ዞን እና በአዳማ ከተማ ግብርናንና አገልግሎትን ለማዘመን የተከናወኑ ሥራዎችን ዛሬ ጎብኝተዋል።

የአዳማ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ሂንሴኔ ሙሐመድ በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ በከተማዋ በተለይ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የሥራ አጥነትን ለመቀነስና የዜጎች የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

በእዚህም ባለፈው ዓመት በከተማዋ 1ሺህ 283 ኢንቨስትመንትን መሳብ እንደተቻለ ያስታወሱት ምክትል ከንቲባዋ፣ ለህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ወይዘሮ ሂንሴኔ ገለጻ፣ በ2015 ዓ.ም በከተማዋ 24 የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች የተገነቡ ሲሆን፤ የአስፋልት፣ የጌጥ ድንጋይ ንጣፍ እና የጠጠር መንገዶችም ተሰርተው ለአገልግሎት በቅተዋል። 

በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመትም የአቅመደካማ ቤቶችን የመገንባትና የማደስ ሥራዎች መከናወናቸውን አስታውቀዋል። 

በተያዘው በጀት ዓመትም የከተማዋን ገቢ ከ5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ወደ 13 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ታቅዶ ወደተግባር መገባቱን ነው የጠቆሙት።

የከተማዋ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ፣ የመሬት አስተዳደርና የመረጃ አያያዝ ስርአቱን የሚያዘምኑ እንዲሁም የሥራ ባህልን ለመለወጥ የሚያግዙ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም አስረድተዋል።

ስማርት የከተማ ፕላንና ልማት ለማከናወን እንዲሁም ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለመስጠት በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑንም ምክትል ከንቲባዋ ተናግረዋል።

ከጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ ዲን ዶክተር በፍቃዱ ቢጨምር በበኩላቸው፣ በጉብኝቱ በጥናትና ምርምር ሊደገፉ የሚገባቸው ውጤታማ ሥራዎች መመልከታቸውን ተናግረዋል።

በተለይ በግብርና መስክ በእንስሳትና ወተት ላሞች እርባታ፣ በዶሮ ልማት፣ በአቮካዶና በሰብል ልማት በአርሶ አደሩ ህይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ያመጡ ውጤቶች ማየታቸውን ገልጸዋል። 

"ኮሌጁ የግብርና ሥራዎችን በጥናትና ምርምር በማጠናከር አርሶ አደሮቹን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ዝግጁ ነው" ሲሉም አረጋግጠዋል።

የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና በበኩላቸው በአዳማ ከተማ እና በምስራቅ ሸዋ ዞን ባደረጉት ጉብኝት ተሞክሮ ሊሆን የሚችሉ ሥራዎችን አይተናል ብለዋል።

"በተለይ በአዳማ ከተማ ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ስርዓት ለመዘርጋትና ሀብቱን በአግባቡ ለማልማት የካዳስተር ስርዓት መተግበሩ ለሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ምሳሌ ይሆናል" ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት አገልግሎት አሰጣጡ በቴክኖሎጂ መታገዙ የህብረተሰቡን የአገልግሎት እርካታ ለማረጋገጥና የከተማዋን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማፋጠን ጉልህ ሚና ይኖረዋል።

የአገልግሎት አሰጣጡ ዲጂታል መሆኑን ተከትሎ በከተማዋ ገቢ እና በኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲሁም በመሬት አያያዝና አጠቃቀም ላይ የታየው ለውጥ አንድ ማሳያ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም