መንግሥት የዋጋ ግሽበትን በዘላቂነት ለማረጋጋት ምርታማነትን ማሳደግና የገንዘብ ሥርጭቱን መፈተሽ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት አለበት - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት የዋጋ ግሽበትን በዘላቂነት ለማረጋጋት ምርታማነትን ማሳደግና የገንዘብ ሥርጭቱን መፈተሽ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት አለበት
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 10/2016 (ኢዜአ) ፦ መንግሥት እንደ አገር የሚስተዋለውን የዋጋ ግሽበት በዘላቂነት ለማረጋጋት ምርታማነትን ማሳደግና የገንዘብ ሥርጭቱን መፈተሽ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት አለበት።
የዋጋ ግሽበት በዓለማቀፍ ደረጃ ባደጉ አገራት ጭምር ፈተና እየሆነ መምጣቱ ይታወቃል፡፡
በኢትዮጵያም ባለፉት ዓመታት በኮቪድ፣ በጦርነት እና ድርቅ፣ የመንግሥት ገቢ ማነስ፣ የወጪ ጫና መብዛት እና በመሳሰሉት ምክንያቶች የተነሳ የኑሮ ውድነት እየጨመረ መጥቷል።
መንግሥት የውጭ ብድር እና እርዳታ ውስን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አብዛኛውን የበጀት ጉድለቱን ከአገር ውስጥ የገንዘብ ምንጮች በሚገኝ ብድር ለመሸፈን መገደዱም ለዋጋ ንረት የራሱ ሚና እንዳለው ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ችግሩን ለመፍታት መንግስት ካለፈው ዓመት መጨረሻ ጀምሮ የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ ያደረገ ሲሆን፤ የአገር ውስጥ የብድር ዕድገት በ14 በመቶ እንዲገደብ መወሰኑም ይታወሳል።
ኢዜአ ያነጋራቸው የምጣኔ ኃብት ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ለመጣው የዋጋ ግሽበት ምክንያቱ የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም እንዲሁም ገበያው ከሚችለው በላይ የገንዘብ ሥርጭት መኖሩ ነው ብለዋል፡፡
በተለይ ምርቶችን በስፋት ከውጭ ማስገባቱ፣ የብር የመግዛት አቅም መቀነስ እንዲሁም የገንዘብ ሥርጭቱ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ማስከተሉን አክለዋል፡፡
በተለይ ሕብረተሰቡ በመሠረታዊነት በሚጠቀማቸው የፍጆታ ዕቃዎች ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ንረት የዜጎችን ሕይወት ፈተና ላይ ጥሎታል ሲሉ የምጣኔ ኃብት ባለሙያዎች ይስማማሉ።
የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የገበያ ሰንሰለቶችን ማሳጠር፣ የመንግሥት ወጪን መቀነስና የብድር አሰጣጥ ሥርዓቱን መፈተሽና የወጡ መመሪያና ደንቦች በአግባቡ መተግበራቸውን መከታተል እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎቹ ጠቅሰዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የንግድ ሥራ ኮሌጅ የኢኮኖሚክስ መምህር ዶክተር ብርሃኑ ደኑ እንደገለጹት፤ በአገሪቱ እየተስተዋለ ያለው የዋጋ ንረት በኢትዮጵያ ካለው የገንዘብ ሥርጭትና ከዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖዎች ጋር የተያያዘ ነው፡፡
ስለዚህም ይላሉ ባለሙያው ገበያው ከሚችለው በላይ የገንዘብ ሥርጭት መኖሩ በአገሪቱ ለተከሰተው የዋጋ ግሽበት ምክንያት በመሆኑ ፤ መንግሥት ባለፈው ዓመት ያወጣውን የአገር ውስጥ የብድር ገደብ በአግባቡ መተግበሩን መከታተል አለበት ብለዋል።
በተጨማሪም መንግሥት የዋጋ ግሽበትን በዘላቂነት ለማረጋጋት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ አኳያ መንግሥት ምርትና ምርታማነትን በማሻሻል ችግሩን ለመቀነስ እያከናወነ ያለውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው ያሳሰቡት።
አላስፈላጊ ወጪን መቀነስ ላይ ትኩረት ተደርጎ ሊሰራበት እንደሚገባ አክለው፤ በተለይ የቅንጦት ዕቃዎች ላይ የተጀመረው ቁጥጥር ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተመራማሪ ተወልደ ግርማ በበኩላቸው፤ የመንግሥት በጀት ጉድለት፤ የሀገሪቱ ወጪና ገቢ ምርት አለመጣጣም ለዋጋ ግሽበት ምክንያት መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈ የተቋማት የማስፈጸም ብቃት ውስንነትና በቀጣናው ያለው አለመረጋጋት ለችግሩ መጉላት ምክንያት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና የተቋማትን የማስፈጸም አቅም ውስንነት ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ አክለዋል።
የዋጋ ንረቱን በዘላቂነት ለማረጋጋት ምርትን ማሳደግ እንደሚገባ በመናገር መንግሥት መነሻዎቹን ሊያጤንና መፍትሔ ሊሰጥ ይገባል ሲሉ ምክረ-ሃሳብ ሰጥተዋል።
በኢኮኖሚው ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን ገንዘብ በመቀነስ እና የግምጃ ቤት ሰነዶችን በመሸጥ ወደ መንግሥት ካዝና የሚገባውን ገንዘብ ማሳደግ መፍትሔ ሊሆኑ እንደሚችሉ አንስተዋል፡፡
መንግሥት ከብድር አሰጣጥ ጋር በተገናኘ አካሄዶቹን በመፈተሽ የዋጋ ንረትን መቀነስ እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡
በተለይም ደግሞ መንግሥት ችግሩን ለማቃለል ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች በአግባቡ መፈጸምና ግቦችን ለማሳካት በትኩረት መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
በነሐሴ ወር 2015 የአገር አቀፍ የዋጋ ግሽበት 28 ነጥብ 2 በመቶ ሆኖ መመዝገቡን የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
አገልግሎቱ በወቅቱ ከተመዘገበው የዋጋ ግሽበት የምግብ ዕቃዎች ዋጋ 26 ነጥብ 5 በመቶ ድርሻ መያዙን የገለጸ ሲሆን፤ ምግብ ነክ ያልሆኑ ደግሞ 30 ነጥብ 7 በመቶ ድርሻ መያዛቸውን ገልጿል፡፡
በአጠቃላይ የዋጋ ግሽበት በሐምሌ ወር ከነበረት 28 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 28 ነጥብ 2 በመቶ መውረዱንም መረጃዎቹ አመላክተዋል።
ኤጀንሲው የዋጋ ግሽበቱ መጠን ዝቅ ያለበት ምክንያት የምግብ ዋጋ ግሽበት አንጻራዊ መረጋጋት ስላሳየ መሆኑም ተገልጿል።